አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

459

ሚያዝያ 10/2011 ጨፌ ኦሮሚያ ዛሬ ከሰዓት እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ጉባዔው አቶ ሽመልስ አብዲሳን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ።

አቶ ሽመልስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።

እንደ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት(ኦቢኤን) ዘገባ  ጨፌው በስብሰባው ዛሬ  የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትንና የክልሉ ፕሬዝዳንት በነበሩት በአቶ ለማ መገርሳ ቦታ እንዲተኩ ነው አቶ ሽመልስን ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጣቸው።

አቶ ለማ ባለፉት ሶስት ዓመታት ክልሉን በፕሬዝዳንትነት የመሩ ሲሆን ዛሬ  የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው በመሾም ቃለ መኃላ ፈጽመዋል።

አቶ ለማ ከ2008 ዓ.ም መጀመሪያ አንስቶ የኦህዴድ ሊቀ መንበርና  የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት የኦዴፓ ሊቀመንበርነታቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መተካቱ ይታወሳል።