የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በምርምር ለመፍታት እየተሰራ ነው

95

ባህርዳር ሚያዚያ 10/2011የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ በምርምር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱን ፖሊሲ ለባለድርሻ አካላት የሚያስተዋወቅ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በእዚህ ወቅት እንደገለፁት ዘርፉ በኢትዮጵያ ከተጀመረ ከ60 ዓመት በላይ ቢሆነውም ብቁ የሰው ኃይልና ቅንጅታዊ አሰራር ባለመኖሩ የሚፈለገውን ያህል ማሳደግ አልተቻለም።

ላለፉት ዓመታት የህዋ ሳይንስ ያለ ፖሊሲ ሲመራ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ዘርፉን በዘላቂነት ሊያሳድግ የሚችል ፖሊሲ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዋ ሳይንስ ለግብርናው ዘርፍ ምቹ የሆኑ መልካ ምድሮችን ለማጥናት፣ የማዕድን አይነቶችን ለመለየት፣ የሃገር ደህንነትን ለመጠበቅና የአየር ጸባይ ሁኔታን ቀድሞ ለመረዳት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሰለሞን እንዳሉት የህዋ ሳይንስ መርሀግብሩን ለማጎልበት የተረቀቀው ፖሊሲ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅዶች የሃገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡

"ግቡ እንዲሳካም ተቋማትን ለእዚሁ ዝግጁ የማድረግና በዘርፉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመመልመል የማሰልጠንና የማስተማር ስራ እየተከናወነ ይገኛል"ብለዋል፡፡"

"መንግስት ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በምርምር የታገዘ ሥራ እየሰራ ነው " ያሉት ዶክተር ሰለሞን፣ ኢትዮጵያም የመጀመሪያዋን ሳተላይት በ2012 ዓ.ም እንድታመጥቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

"የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እስካሁን በፌዴራል ላይ ብቻ ተወስኖ መኖሩ ክልሎች ለዘርፉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ አድርጓቸው ቆይቷል" ፣  ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ መላኩ ጥላሁን ናቸው።

በቀጣይ ተቋሙ በህዋ ሰይንስ ምርምር ላይ በጋራ ለመስራትና ለራሱም ተጠቃሚ ለመሆን ተቋማቸው በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ባለመቻላችን እምቅ የውሃ አቅም ያለባቸውን ቦታዎች ለመለየት ተቸግረናል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞላ ፈጠነ ናቸው።

"እንደ ክልል የውሃ ሀብትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም እንዲጎለብትና በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ በጋራ እንሰራለን" ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ  ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት ከአማራ ክልል የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም