አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት አቀረቡ

128

አዲስ አበባ ሚያዚያ 10/2011በደቡብ ሱዳን አዲስ የኢፌዴሪ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ተፈሪ ታደሰ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አቀረቡ፡፡

አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ትናንት በደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቤተ መንግስት ለአገሪቷ ፕሬዝዳንት ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ ወቅት የሁለቱ አገራት ግንኙነትና በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ ሃሳብ መለዋወጣቸውም ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳናዊያን ያበረከተችው አስተዋጽኦ ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን በማንሳት “ለደቡብ ሱዳን ቀጣይነት ባለው መልኩ ድጋፍ ያደረገ አገር የለም” ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ችግር ለመፍታትኢትዮጵያ የራሷንና የሌሎችን አቅም በማስተባበር እያደረገች ያለችው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎች ማድረግ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው መንግስታቸው በዚህ ረገድ አምባሳደሩ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው በደቡብ ሱዳን ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

አዲሱ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆንና በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እየተደረገ ካለው የጋራ ጥረት በተጨማሪ ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል ያደረጓቸው ስምምነቶች ዳግም ለማነቃቃት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም