የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሚስተር ባምቢስ ቺማስን ጎብኝተዋል

4430

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የባምቢስ ሱፐር ማርኬት ባለቤት ሚስተር ባምቢስ ቺማስን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ሚስተር ባምቢስ በስማቸው ሰፈር የተሰየመላቸው ግሪካዊ አዛውንት ናቸው።

አዲስ አበባ ውስጥ ከመስቀል አደባባይ ወደ ኡራኤል በሚወስደው መንገድ የሚገኘው የባምቢስ ሱፐር ማርኬት ባለቤት ሚስተር ባምቢስ ቺማስ ሰሞኑን ጤንነት ባይሰማቸው፤ “ስራዬ ላይ ችግር ገጠመኝ” ቢሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአካል ሄደው ጎብኝተዋቸዋል።

በጉብኝታቸው ወቅትም ለሚስተር ባምቢስ ጥሩ ጤንነት መመኘታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዶክተር ወርቅነህ ባምቢስ ሱፐርማርኬት በሚገኘው ቢሮአቸው ሄደው የ87 ዓመቱን ባምቢስ እና የ78 ዓመት ባለቤታቸውን እሌኒ ቺማስን ባነጋገሩበት ወቅት “እናንተ ከእኛ እንደ አንዱ ናችሁ፤ እናንተ የኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም የእናንተ ናት” ብለዋቸዋል።

ሚስተር ባምቢስም ለዶክተር ወርቅነህ “ግሪክ ደሜ፤ ኢትዮጵያ ልቤ ናት በዚህ እድሜዬ ስለራሴ ምንም አልጨነቅም፣ የማስበውም የምጠበበውም ስለ ኢትዮጵያ ክብር ነው” ብለዋል።

በግሪክ ርዕሰ መዲና አቴንስ የተወለዱት ሚስተር ባምቢስ በኢትዮጵያ መኖር ከጀመሩ 67 ዓመት እንደሆናቸውና ባለቤታቸው እሌኒ ቺማስ አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ መወለዳቸውን መግለጫው አትቷል።

ሚስተር ባምቢስ ቺማስ ከሱፐር ማርኬት ንግዳቸው በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ስራ የሚታወቁ ሲሆን ባለፈው ዓመት ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ለተባለው ማህበር የአንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።