በብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር አዲስ አበባ ፖሊስ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል

282

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2011 ዛሬ በደሴ ከተማ በተጀመረው የሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር አዲስ አበባ ፖሊስ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡

በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የሚደረግባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዛሬ ውድድሩ ሲጀመር በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች የፍጻሜ ጨዋታ የአዲስ አበባ ፖሊሷ ፈለቀች ሰይፉ የደሴ ከተማዋን ተወዳዳሪ ፌቨን አህመድን በበቃኝ አሸንፋለች።

ውጤቱንም ተከትሎ አዲስ አበባ ፖሊስ የቦክስ ክለብ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱን ተናግረዋል።

ትናነት ከተካሄዱ የፍጻሜ ጨዋታዎች በተጨማሪ በወንዶች 49፣ 56፣ 60፣ 69 እና 70 ኪሎ ግራም በ48 ኪሎ ግራም ሴቶች የማጣሪያ ውድድሮች እንደተካሄዱም ጠቅሰዋል።

ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭ ማስፋትና በነሐሴ 2011 ዓ.ም በሚካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን መመልመል የውድድሩ አላማ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንና የመጀመሪያው ውድድር ህዳር 2011 ዓ.ም በድሬዳዋ እና ሁለተኛው ዙር በወላይታ ሶዶ ከተሞች መካሄዱ ይታወሳል።

አራተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።