እስራኤል ለኢትዮጵያ የፍራፍሬ ልማት ድጋፏን ታጠናክራለች--- አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ

128
ባህር ዳር ግንቦት 27/2010 ኢትዮጵያ ለፍራፍሬ ያላትን ምቹ የእርሻ መሬት በአግባቡ እንድትጠቀም እስራኤል ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጰያ የሀገሪቱ አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ገለጹ። በእስራኤል እና በአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅቶች ድጋፍ ከ900 ሺህ ብር በላይ ወጪ በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በፀሓይ ኃይል የሚሰራ የጠብታ መስኖ ሙከራ ተግባር ትናንት ተጎብኝቷል። አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ በዚያ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ለአትክልትና ፍራፍሬ ምቹ የሆነ የከርሰና ገጸ ምድር ውሃ ከተስማሚ የአየር ንብረት ጋር የታደለች ሀገር ናት። ይሁን እንጂ አርሶ አደሩ በዘርፉ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂ ባለመጠቀሙ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እያገኘች እንደልሆነ ተናግረዋል። "አርሶ አደሮቹ ፍራፍሬን እንዴት ማምረት እንዳለባቸው በማሰልጠንና በቴክኖሎጂ የካበተ ልምዷን በማካፈል እስራኤል የጀመረችውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች "ብለዋል። የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እያሱ አብረሃ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ግብርናውን በማዘመን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ለማሳደግ አርሶ አደሩን በማሳተፍ ትኩረት ሰጥታ እየተሰራች መሆኑን ገልጸዋል። መንግስትም የአርሶ አደሩን አቅምና ክህሎት በማሳደግ ዘመናዊ የአስተራረስና አመራረት ዘዴን ለመጠቀም ትኩረት አድርጎ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይ ሀገሪቱ ለፍራፍሬ ልማት ካላት አመቺነትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አኳያ እየተጠቀመች እንዳልሆነ ጠቅሰው" በዘርፉ እንደእስራኤል የተካበተ ልምድ ካላቸው በመውሰድ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እየሰራች ትገኛለች "ብለዋል። በአማራ ክልል 860 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይተነው እንደሻው ናቸው። አርሶ አደሩ ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ የተሻሻሉ የግብርና  አመራረት ዘዴዎችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በስልጠና የመደገፍ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "በሙከራ ደረጃ በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በጠብታ መስኖ በክላስተር ማልማት የተጀመረውን ስራ በቀጣይ ወደ ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ለማሳደግም እየተሰራ ነው" ብለዋል። ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል ወጣት ጥላሁን ፈቃዱ በሰጠው አስተያየት በመስኖ  እያለማው ካለው የአትክልት ችግኝ ሽያጭ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡ አርሶ አደር መለሰ አይሸሹም በበኩላቸው ከበቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በኩታ ገጠም የአቡካዶ ችግኝ እያዘጋጁ ሸጠው ለመጠቀም ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በፀሓይ ኃይል የሚሰራ የጠብታ መስኖ ሙከራ ተግባር ትናንት የተጎበኘው በአራት ነጥብ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለው የአቮካዶ አትክልት ነው። በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር፣ የፌዴራልና የክልል ስራ ኃላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተገኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም