የጀርመኑ ባየርሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ለፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ስማቸው የተጻፈበትን የክለቡን መለያ አበረከተ

103

አዲስ አበባ ሚያዝያ 09 /2011የጀርመኑ ባየርሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ለፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ስማቸው የተጻፈበትን የክለቡን መለያ በስጦታት አበረከተ።

ክለቡ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ለመክፈት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ፈርሟል።

የባየርሙኒክ እግር ኳስ ክለብ መቀመጫ የሆነችው የባቫሪያ ግዛት ሚኒስትር ማርከስ ሶደር “ሣህለወርቅ “ የሚል ጽሁፍያረፈበትን የክለቡን መለያ ለፕሬዚዳንቷ አበርክቷል፡፡

የክለቡ አምባሳደር የሆነው የቀድሞው ተጫዋች ጂኦቫኒ ኤልበር ፤ ባየርሙኒክ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ልማት ላይ ለመስራት በአፍሪካ የመጀመሪያውን የታዳጊዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊከፍት መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክለቡ አመራር ልዑክ በኢትዮጵያ ሊገነባ ከታሰበው አካዳሚ ጋር በተያያዘ በቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ለመምከርና ታዳጊዎችን ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ተገልጿል።

በዚህም እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆነና በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ውድድራቸውን እያካሄዱ በሚገኙ 8 ክለቦች መካከል የአንድ ቀን የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰላም እግር ኳስ ክለብ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሰውነት ቢሻው እግር ኳስ፣ ደደቢትና ኢትዮጵያ መድን በሁለት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ይህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ለማየትና ግንዛቤ ለመጨበጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ክለቡ የሚከፍተውን የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለሶስት አመት የሚዘልቅ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የክለቡ አምባሳደር ጂኦቫኒ ኤልበር  "ህዝቡ ለእግር ኳስ ትልቅ ፍቅር እንዳለው አስተውያለሁ"  በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለመደገፍም ወደ አካዳሚው የሚገቡ ታዳጊዎች ስለ እግር ኳስ አጠቃላይ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚፈልግም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ከባየር ሙኒክ የሚመጡ አሰልጣኞች ታዳጊዎችን በእግር ኳስ ክህሎት ለማብቃት ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩና በቀጣይም በባየርሙኒክ እና በአጠቃላይ በአውሮፓ የሚጫወቱበትን ዕድል ለማመቻቸት ይሰራል ተብሏል።

አካዳሚው መቼ እንደሚቋቋም፣ ምን ያህል ታዳጊ በውስጡ አቅፎ እንደሚይዝ እና መቼ ስልጠናውን እንደሚጀምር ወደፊት እንደሚያሳውቁም ተናግረዋል።

ባየርሙኒክ በጀርመን ቡንደስሊጋ ከሚገኙ አንጋፋ ክለቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ማሰልጠኛ አካዳሚውን በኢትዮጰያ ሲከፍት በአለም ላይ የከፈታቸውን ተመሳሳይ የእግር ኳስ አካዳሚዎቹን ስድስት ያደርሰዋል፡፡

ክለቡ  ቀደም ሲል የእግር ኳስ መማሰልጠኛ አካዳሚዎቹን  በአሜሪካ፣ ቻይና፣ ታይላንድ፣ ጃፓንና ሲንጋፖር ከፍቷል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም