ባለፈው አንድ አመት የትራንስፖርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ ተሰርቷል- የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን

65

አዲስአበባ ሚያዚያ  9/2011 በለውጥ  ጉዞው ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን  በመለየት፤ ችግሮቹን ለመፍታት በተሰራው ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን ነው የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የገለጸው።

የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግዛው ዳኛው ለኢዜአ እንዳሉት በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ችግሮቹን ለመቅረፍ  ወደ ስራ ተግብቷል፡፡

በዚህም የትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የአደረጃጀት ቅንጅትና የአሰራር ችግር፣ የትራፊክ አደጋ፣ የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅና አገልግሎቱ ዘመናዊ  አለመሆን በዘርፉ የሚታዩ  ዋና ዋና ችግሮች ተብለው መለየታቸውንም  ጠቅሰዋል።

ችግሮቹን ለመፍታትም ባለፈው አንድ ዓመት የስራ አካባቢን ምቹና ሳቢ በማድረግ፤ የተገልጋይን እና የሰራተኛውን እርካታ ማሳደግ የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በተለይ  አላሰራ ያሉ የአሰራር መመሪያዎችን የመለየትና  ክልሎች ጋር የነበረውን የላላ ግንኙነት ማጠናከርና  የባለድርሻ አካላትን መለየት የተቻለበት ነው ብለዋል።  

በዘርፉ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ ለመሥራት በዚህ ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ ተጀምሯል ያሉት አቶ ግዛው  አስራ ስምንት አገልግሎቶችን በኦንላይን ቴክኖሎጂ መስጠት መጀመሩን ነው ያስረዱት።

በዘርፉ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ድርሻ ያለው  ዘመናዊ ዳታ ቤዝ የማደራጀት ስራ  እየተከናወነ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመንጃ ፍቃድና ዘጠኝ መቶ ሰባ  በላይ የተሸከርካሪ መረጃዎች በዳታ ቤዙ መግባታቸውን ገልጸዋል።  

ባለፈው አንድ ዓመት በተሰራው ስራ በሃምሳ ስምንት የተሸከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ በተካሄደው የማጣራት ሥራ ሰላሳዎቹ ከመስፈርት ውጭ ሆነው በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።

ከሃምሳ ስምንት የተሸከርካሪ ምርመራ ተቋማትም ሰላሳ ስድስቱ ብቻ  ብቁ ሆነው መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

ከመንገድ ደህንነት ጋር በተያያዘም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠቱንና በሰባት  አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ጥፋተኛ የሆኑ ግለሰቦች ላይ  እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የፍጥነት ወሰን መገደቢያ መሳሪያ ተግባራዊ ለማድረግ መመሪያ መዘጋጀቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤  መሳሪያው  የሚቀርብበበትን  ሁኔታ ለማመቻቸት ከአቅራቢ ባለሃብቶች ጋር እየሰሩ  እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

መነሪያዎችን የማዘመንና ለተገልጋይ ምቹ የማድረግ ስራ በዚህ አመት መጀመሩን  ያመለከቱት አቶ ግዛው፤ ለአብነትም  የቃሊቲ መነሀሪያ በአራት መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን ብር ለመገንባት መሰረት ድንጋይ መጣሉን አመልክተዋል፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት የላምበረት መነሀሪያ ከፍተኛ እንግልትና ተሽከርካሪዎች የሚጨናነቁበት እንደነበር የተናገሩት የመነሀሪያው ቡድን መሪ  አቶ ጌታሁን ቸሩ፤  በላፈው  አንድ አመት በተሰራው ስራ በቂ ማረፊያ መገንባቱና ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ አካላት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የመኪና አሽከርካሪ  የሆኑት አቶ ቢተው አሰፋ በትራንስፖርት ዘርፉ ጅምር ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ስምሪት ላይ የሚታየው ህገ ወጥነት፣ የሙስና ችግርና የአገልግሎት አሰጣጥ አለመቀላጠፍ በቀጣይ ልታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።  

ዘርፉ ካለበት ችግር አንጻር አሁንም በርካታ ተግባራት ማከናወንን ይጠይቃል ያሉት  የኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተሩ በቀጣይ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመንና  አላሰራ ያሉ ህጎችን የማሻሻል ሥራ ይሰራል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም