በዞኑ እየተካሄደ ባለው የመኸር እርሻ 39 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎና በማሽላ ዘር ተሸፍኗል

77
ነቀምቴ ግንቦት 27/2010 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን እየተካሄደ ባለው የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ 39 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎና በማሽላ ዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሞርካ ፉታሳ እንደተናገሩት በዘር የተሸፈነው በ2010/2011 የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ315 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ነው። እስካሁን ከ263 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶና ለስልሶ ለዘር ሥራ መዘጋጀቱን የገለጹት ኃላፊው ለምርት ዘመኑ ከ209 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ግብዓት ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። እስካሁን ድረስ ከ98 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 9 ሺህ 981 ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን የገለጹት አቶ ሞርካ፣ በመኸር እርሻው በዋናነት ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳና መሰል የሰብል አይነቶች እንደሚለሙ ተናግረዋል። "በምርት ዘመኑም ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷልም" ብለዋል። በጅማ ገነቲ ወረዳ የጨሮ ጎበኖ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አበራ ማታቤ በሰጡት አስተያየት በመኸር እርሻ ለማልማት ካቀዱት ሦስት ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሹን በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ጠቁመዋል። አርሶ አደር አበራ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናብ ለእርሻ ልማት ሥራው ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ ቀሪውን መሬት በዘር ለመሸፈን ተዘጋጅተዋል። አራት ሄክታር ማሳቸውን ደጋግመው ሲያርሱና ሲያለሰልሱ መቆየታቸውን የገለጹት በወረዳው የበልበላ ቦርጎ ቀበሌ አርሶ አደር በላይ በቀለ በበኩላቸው  እስካሁን ድረስ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ መዝራታቸውን አመልክተዋል። በዞኑ የአቤ ደንጎሮ ወረዳ የኢዶ ኩሳ ቀበሌ አርሶ አደር ገበየሁ አብድሳ በበኩላቸው "በግብርና ባለሙያ ምክር በመታገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራሁ ነው" ብለዋል። ባለፈው ዓመት በምርት ግብዓት እጥረት ያጡትን ምርት ዘንድሮ ለማካካስ የተሻሻለ የግብርና አሰራር ተጠቅመው ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም