በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር የሚስተዋለውን ግጭት ለማስቆም እየተሰራ ነው

326

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2011 በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር የሚስተዋለውን ግጭት ለማስቆም ኢትዮጵያ በቅድሚያ በሞያሌ አዋሳኝ ላይ ያለውን ውስጣዊ ግጭት መከላከል ላይ ማተኮሯን ገለጸች።

በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር በሞያሌ አካባቢ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት  የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዘይኑ ጀማል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ከሰባት ዓመታት በፊት በሁለቱ አገሮች አከባቢ ያለው ግጭት መልኩን እየቀየረ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።

ከዛ በኋላም በየዓመቱ በሚባል ደረጃ አካባቢው የተለያየ አይነት ግጭቶችን በማስተናገዱ በርካታ ዜጎች ለህልፈተ ህይወትና ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በአከባቢው ታጣቂ ኃይሎች በሰርጎ ገብነት ከተቀላቀሉ በኋላ የሚደርሰው ጥፋት በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡንና ይህም በአካባቢው ሠላም እንዲርቅ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት ከለውጥ ጊዜ አንስቶ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር እርቅ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ያም ሆኖ በአገር ወስጥ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ወሰን መካከል የተከሰተውን ግጭት ለኢትዮጵያና ለኬንያ ድንበር ግጭት ተጨማሪ አባባሽ ሁኔታ እንዳያስከትል ግጭት የማርገብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም ግጭት ለማርገብ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በኬንያ የማንዴራ አከባቢ አስተዳደሪ አሊ ሮባም በኬንያ በግጦሽ መሬትና በቀንድ ከብት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ውስጣዊ ግጭት መኖሩን ለአብነት አንስተዋል።

ያም ሆኖ ከማኅበረሰብ አባላት ጋር በተደረገው ተደጋጋሚ ውይይት እነዚህን ችግሮች በመፍታት አሁን ላይ ሠላም መውረዱን ገልጸዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለይም በድንበር አከባቢ የሚከሰቱትን ችግሮች ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራርን መሰረት ያደረገ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የምክክር መድረኩ በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።