በመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ አራት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች

100

ሚያዝያ 9/2011 በአፍሪካ ወጣቶችና ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ አራት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች

በኮትዲቫር አቢጃን የአፍሪካ የወጣቶችና ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ  አራት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች።

ከአራቱ ሜዳሊያዎች ውስጥ አንዱ ወርቅ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው።

ለአምስ ቀናት  በሚቆየው  የአፍሪካ ከ20 ዓመትና ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 39 ሴትና 43 ወንድ፤  በድምሩ 82 አትሌቶችን  በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀትና በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባረት በሆኑት በውርወራና ዝላይ ስፖርቶች  ትካፈላለች።

ይህ ሻምፒዮና ትናንት ሲጀመር ኢትዮጵያ በወንዶች በ10 ሺህ ሜትር፣ በ1ሺህ 500 ሜትር፣ በስሉስ ዝላይ እና በሴቶች ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር ሩጫና በስሉስ ዝላይ ተካፍላለች።

ከእነዚህ ውድድሮች በሴቶች ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች ውድድር በ3 ሺህ ሜትር አትሌት አለሚቱ ታሪኩ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ  ማምጣት ችላለች።

በዚሁ ርቀት አትሌት ፀሀይ ሀይሉ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችላለች።

በሴቶች ከ18 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ደግሞ አትሌት ሰንበቴ ሮቢ  ለሀገሯ የብር ሜዳሊያ ማምጣት  ችላለች።

በወንዶች ከተደረጉት ውድድሮች መካከል ደግሞ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ውድድር አትሌት ይሁን ፋንታሁን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ለሀገሩ ማምጣት ችሏል።

በ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ የተካፈሉት አትሌት ደረጀ አዱኛና አትሌት ቢተው አደም አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቃቸው ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም