የፌዴራል ፍትህ ተቋማት ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ ነው

60
አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን የፌዴራል የፍትህ ተቋማት ገለጹ። 8ኛውን አገር አቀፍ የፍትህ ሳምንትን አስመልክቶ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የፌዴራል ፍትህ ተቋማትን ያሳተፈ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉ ተቋማት "አዲስና ቀደም ሲል ተግባራዊ የተደረጉ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው" ብለዋል። በዚህም ከተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችንና ብልሹ አሰራሮችን ለመቀነስ እንደተቻለ ነው የሚናገሩት። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ልዑል ሐጎስ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት ለማግኘት የምዝገባና የወረፋ ስርዓቱን በኮምፒውተር የተደገፈ በማድረግ "ከሰው ንኪኪና ከብልሹ አሰራር ነጻ ለማድረግ መቻሉን" ተናግረዋል። በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ሱፐር ኢንቴንዳንት ወንድወሰን አበበ የጣት አሻራ በመጠቀም በተደጋጋሚ ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚገቡ ታራሚዎችን ለመለየት፣ ለማረምና ሌሎች ላይ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለመቀነስ ተችሏል ብለዋል። ለአብነትም በዝዋይና በሸዋ ሮቢት ያሉ ታራሚዎች ባሉበት ሆነው የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እንዲከታታሉ ለማድረግ እንደተቻለም አክለዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኝነት ክፍል የህትመት ሚዲያ ኃላፊ ሳጅን ዳዊት እርገጤ በበኩላቸው ተጠርጣሪዎች ቃል በሚሰጡበት ወቅት በካሜራ በመቅረጽ ከተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ መከናወኑን ለመቆጣጠር ምቹ መንገድ መፈጠሩን ነው የገለጹት። ተጠርጣሪዎችን በጊዜያዊነት የማቆያ ክፍሎችም ካሜራ በመግጠም "በክፍሎች ውስጥ የሚፈጠሩ የግብረ ሰዶም ወንጀሎችንና ግጭቶችን ለመቆጣጠር መቻሉንም" ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የህዝብ ግንዛቤ ማሳደጊያ ክፍል ማስተባባሪያ ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ግዛው አረጋ የትራፊክ ቁጥጥሩን ለማሻሻል የአልኮል መመሪያና የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ስራ ላይ ማዋላቸውን ይናገራሉ። በዚህም "በትራፊክ አደጋ ሳቢያ የሚከሰተውን ሞትና ከባድ አደጋ በመቀነሱ ረገድ ለውጥ መገኘቱን" ገልጸዋል። በቀጣይ ደግሞ የትራፊክ ፖሊሶች የደንብ ጥሰት የፈጸሙ አሽከርካሪዎችን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው በመጠቀም እንዲቀጡና የመንጃ ፍቃድ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር ስራ ላይ እየዋልን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም