ምክር ቤቱ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ መራ

119

ሚያዝያ 8/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው የ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 33ኛ መደበኛ ስብሰባው  በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  በተባባሪነት ደግሞ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ረቂቅ አዋጁ ስድስት ክፍሎችና  ሰላሳ አንቀሶች ያሉት ሲሆን የተከለከሉ ተግባራት፣ የጦር መሳሪያ ፈቃድ የማይሰጣቸው ተቋማት፣ የጦር መሳሪያ የሚሰጥበት ሁኔታና መስፈርት፣ የጦር መሳሪያ ስለሚታገድበት፣ ስለሚሰረዝበት ሁኔታ፣ በልማድ ለታጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የጦር መሳሪያ ፈቃድ ስለሚሰጥበት መስፈርት እንዲሁም የወንጀል ቅጣትና ሌሎች ድንጋጌዎችን አካቷል።

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የአዋጁን አስፈላጊነት ሲያብራሩ በአሁኑ ሰዓት በህገ ወጥ መንገድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ በአገሪቱ እየተዘዋወረ መሆኑን በማንሳት የአገርን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የጦር መሳሪያ ዝውውር አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ አስፈልጓል ብለዋል።

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ የጦር መሳሪያ  ፈቃድ የተሰጠው ሰው ሊኖረው የሚገቡ ህጋዊ  ሁኔታዎችንም  አካቶ  እንደተዘጋጀም አብራርተዋል።  

ፈቃድ የተሰጠው አካል የጦር መሳሪያውን ለሌላ ሶስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት እንደማይችልም ረቂቅ አዋጁ በዝርዝር እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።

አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የአዋጁን አስፈላጊነት ከግምት በማስገባት ምክር ቤቱ ዝርዝር ውይይት በማድረግ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታው  ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ  አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር ማየት አለበት ያሏቸውን ድንጋጌዎችና አንቀጾች  ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከነዚህም መካከል በተለምዶ የጦር መሳሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑና የጦር መሳሪያ የያዙ ሰዎች፣ የጸና ፈቃድ ሳይኖረው የጉዳት አድራሽ እቃ ወደ አገር ማስገባትና ማስወጣት፣ መያዝ ወይንም ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መደለል፣ መሸጥ ወይንም መግዛት፣ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝና ማምረት የሚሉት ድንጋጌዎች በዝርዝር መታየት አለባቸው ብለዋል።

ከጦር መሳሪያ ጋር በተገናኘ የወንጀል ተጠያቂነትን በሚመለከት የተቀመጠው ቅጣት ቀላል በመሆኑ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በትኩረት እንዲያየው የምክር ቤቱ አባላት በውይይታቸው አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ  ከተወያየበት በኋላ የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምሮ ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  በተባባሪነት ደግሞ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች እና በንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ከጅቡቲና ህንድ መንግስት ጋር ያደረገችውን የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል።

በአገራቱ መካከል የተደረገው የሁለትዮሽ የንግድ ትብበር ስምምነት የኢትዮጵያ ምርቶች በጅቡቲና ህንድ  ሲያልፉ ከሌሎች አገሮች ምርቶች እኩል እንዲያልፉ እና የተለየ ግዴታ እንዳይጣልባቸው የሚያደርግና ትብብርን የሚያጠናክር በመሆኑ ምክር ቤቱ አስፈላጊነቱ ላይ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም