ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀን በዓልን እንድታዘጋጅ ተመረጠች

292

ሚያዝያ 8/2011 ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 የሚካሄደውን “የአፍሪካ ቀን” በዓል እንድታዘጋጅ ተመረጠች

ተቀማጭነታቸውን ናይሮቢ ያደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ኮሚሽነሮች ዛሬ  ባካሄዱት ስብሰባና ምርጫ በዓሉን ለማክበር በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው የገለጹት።

“የአፍሪካ ቀን” በዓል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበትን ቀን በማስመልከት እ.አ.አ ‘ሜይ 25 ቀን 2019’ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው።

የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ ቡድን በናይሮቢ ባለፈው ዓመት በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲዘጋጅ ላደረገችው አልጄሪያም ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል።

 በኬንያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮውን በዓል ስኬታማ ለማድረግም ኢትዮጰያ ለአፍሪካ ሕብረት መመስረት ያበረከተችውን አስተዋፅኦ ሕብረቱን ለማጠናከር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ አጠናክራ ትቀጥላለች።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ቀንን በልዩ ሁኔታ እንደምትመለከተውም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ቀን” የአፍሪካን መራራ የነፃነት ትግልና ብሩህ ተስፋ በማሰብ የሚከበር በዓል ሲሆን፤ አፍሪካውያን ባህላቸውን፣ ትውፊታቸውን እና ስልጣኔያቸውን ለመላው ዓለም የሚያስተዋውቁበት በዓል ሆኖ እንደሚከበር ይታወቃል።