ታራሚ ጥቅሶች!

4220

አየለ ያረጋል /ኢዜአ/

ግድግዳዎቻችን የመጠለያ ግብዓቶች ብቻ አይመሰሉም፤ የሐሳብ ሰሌዳም ጭምር እንጂ። በተቋማትና ጎዳናዎች ስናልፍ ስናገድም ከስርቻ እስከ  አደባባይ የግድግዳ/አጥሮች ሰሌዳ ላይ ጽሁፎችን መመልከት ብርቅ አይደለም። እናም ‘ግድግዳችን የፅህፈት ብራና ሆኗል እንዴ’ ያስብላል። በርግጥ የተለያዩ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ የግድግዳ ላይ ትዕምርቶች በአብዛኛው በሕገ ወጥ መልኩ የሚሳሉና የሚጻፉ ግልጽ መግባቢያዎች እንደሆኑ ያትታሉ። እኔ ግን ትኩረቴ ተነባቢ የፊደላት ጽሁፎች ላይ ነው።

የኢትዮጵያ የግድግዳ ላይ ፅሕፈት(ግራፊቲ) ጥንታዊ መሆኑ እሙን ነው፤ አክሱማዊያን በድንጋይና ቋጥኝ ላይ ፍቀው መልዕክት አስተላልፈዋል፤ ሳባዊያን ፈደላትን ቀርጸዋል። ዛሬም ከመጸዳጃ ቤቶች እስከ ታላላቅ ተቋማት የግንብ ግድግዳዎች በተለያዩ የጽህፈት ግብዓቶች ተለቅልቀው ይስተዋላሉ። ‘ሃሳብን በግድግዳ ላይ ማስፈር ከጥንተ አክሱማዊያን የወረስነው ባሕል ይሆን እንዴ’ ያስብላል።

የግድግዳ ላይ ጽሁፎች በታይታ የሚጻፉ ባይጠፉም በብዛት በስውር የሚጻፉ፤ ደራሲያቸው ወይም ሰዓሊያቸውም የማይታወቁ ናቸው። በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ እነዚህ ጽሁፎች የአካባቢውን ሁናቴ ወይም የትውልዱን ማንነት ገላጭ ተደርገው ይወሰዳሉ። ጭብጠ-ብዙ ናቸው! ስለ ፍቅር፣ ፖለቲካዊ ንቅናቄ፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት… ወዘተርፈ።

በዚህ ሰሞን 211 ኪሎ ሜትር(በጎግል ካርታ ስሌት) አቋርጨ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ነበርኩ። በነገራችን ላይ በዚህ ቅርብ በሚባል ርቀት መልክዓ ምድሩ ጉራማይሌ፤ ገጸ-ምድሩም ‘አለምዬ ሶራ’ ነገር ነው። የባሶና ወራና ወረዳ(ደብረ ብርሃን ዙሪያ ገባ) ያው ሜዳማ፤ የምድሩ ሁኔታም ደረቃማ ነው፤ የወርኃ ግንቦት ካፊያ ገና አላለመለመውም። አለፍ እንዳልን ኮረብታማው ጣርማበር ወረዳ(የጣረማ በር ዋሻ ዙሪያ ገባ) ይገኛል። አካባቢው ሲበዛ ደጋማ ነው፤ ምድሩም ሐመልማላዊ ነው። ግንቦት ወር ሳይሆን ወርኃ መስከረምን ያስታውሳል። የገብስ፣ የጤፍ፣ የስንዴ የአደንጓሬ፣ የበቆሎ….ሌላም አዝእርት ዓይን ይስባል። የኮረብታው ልምላሜ አረንጓዴማነትና የሳሮች አይነት የባሌ ተራሮች ፓርክን ይመስላል። የጣርማ በር አቀበትን ወርደን፤ የዳኛቸው ወርቁ ቀዬን ደብረ ሲናን አልፈን የተወሰነ እንደ ሸመጠጥን የቀወት መልክዓ ምድር ያፈጣል። የቀወት ወረዳ(ሸዋሮቢት ዙሪያ ገባ) በርሐማ ነው። አዋሽ አርባን ወይም አርማጮን ያስታውሳል። ከጣርማ በር በመልክዓ ምድራዊም ሆነ በአየር ንብረት በምንም አይመሳሰሉም። የቀወት ኮረብታዎች ምድረ በዳ፤ የጣረማበር ኮረብታዎች ደግሞ ምድረ ሐመልማል ናቸው። የማህበረሰቡ ኑባሬም(አለባበስ፣ አነጋገር፣ አኗኗር) ቢሆን ከሸዋ ይልቅ ወደ ደቡብ ወሎ ያደላ ይመስላል። ይሄ ነው ጎራማይሌነት፤ ‘አለምዬ ሶራ’ ማለት። ግን ያው ኢትዮጵያዊ መልኩን… ነውና ያው ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ። የሸዋሮቢት ከተማ አንዱ መለያዋ በከተማዋ የሚገኘው ‘የተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት’ ይመስለኛል። ከ50 ዓመታት በፊት በራስ አበበ አረጋይ አማካኝነት ለወታደራዊ ማዘዣነት እንደተመሰረተ ይነገራል።  ዛሬም ድረስ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጥላ ስር ከሚተዳደሩ ግዙፍ ማረሚያ ቤቶች አንዱ ነው። በማረሚያ ቤቱ ሕግ ታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች የማየት ዕድል ባይገጥመኝም በታራሚዎች የስራ ክፍሎች(ታራሚዎች በዕንጨት ስራ፣ በሽመና፣ በቅርጻ ቅርጽ፣ በብረታ ብረትና ሌሎች የሙያ መስኮች መሰማራታቸውን) የመታዘብ ዕድሉ ነበረኝ።

ከትዝብቴ ውስጥ ቀልቤን የሳቡት ከላይ የጠቀስኩት የግድግዳ ላይ ጽሁፍ ጉዳይ ነበር። የግድግዳ ላይ ጽሁፎች/ጥቅሶቹ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስነ ልቦናና ማንነት አንጸባራቂ ከሆኑ ታራሚዎቹ ምን ጽሁፎችን አሰፈሩ በሚል ዕሳቤ ነው ትኩረቴ ወደ ግድግዳ ላይ ሃሳቦች የተወረወረው። ከተነባቢ ግራፊቲዎች ውስጥ አምስቱን በማስታወሻዬ አስፍሪያለሁ። ከነዚህ ሃሳቦች ተነስቶ ምናልባት የሕግ ታራሚዎችን ስነ ልቦና መገመት ይቻል ይሆናል።

ቀዳሚው ጽሁፍ ‘God never let you down!’ የሚል ነው። ‘ምንም ቢሆን እግዚአብሄር ጥሎ አይጥልህም’ እንደማለት ነው። ጥቅሱ ቀለም የዘለቀው ታራሚ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ሌላ ሃሳብም ያጭራል። መቸም አንድ ግለሰብ ስለአንድ ልዕለ ኃይል(Superpower) ህልውና ካመነ ሐይማኖት የሚባል ነገር እንደሚኖረው መገመት ይቻላል። የትኛውም ሃይማኖት ደግሞ ኃጢያትን(ወንጀልን) ኮናኝ ነው። በዚህ ማረሚያ ቤት የሚገኙ አብዛኛው ታራሚዎች የስርቆት ወንጀል ፍርደኞች ናቸው። ለምሳሌ በመጽሃፍ ቅዱስ ‘አትስረቅ’ ከአስሩ ትዕዛዛት አንዱ ወንጌላዊ ትዕዛዝ ነው። እናም የስርቆት ወንጀል አንድ ታራሚ እግዚአብሄርን ተስፋ ካደረገ የእግዚሄርን ትዕዛዝ መጠበቅ ግድ ይለዋል። እናም ጥቅሱ ታራሚዎቹ በወንጀላቸው ተጸጽተው፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገዋል ማለት ነው ያስብላል። በርግጥ እግዚአብሔር የለም፤ ‘እምነታችን ህብረተሰባዊነት ነው’ ሲሉ የነበሩ የደርግ ባለስልጣናት ከማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ‘አክራሪ ሐይማኖተኛ’ እንደሆኑ ታዝበናል።

ሁለተኛው ድግሞ “Together to change”ይላል። “ለመለወጥ እንተባበር” የሚል አንድምታ አለው። ምናልባት ‘ምን አይነት ለውጥ’ ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ እንደ ጸሐፊው ዓላማና ሃሳብ ሊወስን ይችላል። ግን በማረሚያ ቤት ዓውድ ሲተነተን ከባሕሪ ለውጥ ጋር ማያያዝም ይቻላል። ማረሚያ ቤት ጥፋተኞችን ከተለያዩ ደባል ሱሶች ማውጣትና ቅንና ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲይዙ ማድረግ አንዱ ግብ ስለሆነ ከዛ ዕውድ ማየት ይቻላል።

“ጤና ካለ ሁሉም አለ” ሶስተኛው ጥቅስ ነው። መቸም የጤናን አስፈላጊነትና የሁሉም ነገሮች ቁንጮነት ‘ጤና ያጣን ሰው’ ያህል የሚያውቀው ያለ አይመስለኝም። እናም በማረሚያ ቤት ሰዎች አተያይ ‘ጤና ካለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፤ ታርመን እንወጣለን፤ ዋናው ጤናችን አይጓደል’ ማለታቸው መሰለኝ።

በተለያዩ ዘመናት ኃያላን ተነስተዋል። መልሰውም ከስመዋል። የተናቁት የናቃቸውን መርተዋል። በዚህ የነገሮች መፈራረቅ የዕድሜ ጸጋ የተሰጠው ግለሰብ መታዘቡ አይቀርም። የነገሮች ዑደት ታዝቦም “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” ብሎ መተረቱ አይቀርም። እናም አራተኛው የታራሚዎች ጥቀስ “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” የሚል ነው። በርግጥ ጥቅሱ አገረሰባዊ ነው። ዋናው ግን ከማህበረሰቡ ዕልቆ-ቢስ ስነ ቃሎች መርጦ መጠቀም የታራሚውን ውስጣዊ ማንነትን ሊያንጸባርቅ ይችላል።

‘የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም’ ሲባል ‘ጊዜ ያጀግናል፤ ያዋርዳል፤ እኛ ዛሬ ቀን ጥሎን ማረሚያ ቤት ብንሆንም ትልቅ ሰዎች ነበርን፤ ወይንም ወደፊት ጀግና እንዳንሆን የሚያግደን ነገር አይኖርም። ጀግንነት በጊዜ የሚሰፈር እንጂ ሰው በራሱ ጀግና ሆኖ አይፈጠርም’ ማለታቸው ይሆን የሚል ሀተታ ሊሰጠው ይችላል።

“ልብ ይበሉ!” ማስታወሻዬ ላይ በመጨረሻ ያሰፈርኳት ጥቅስ ነች። ለማሰብ፣ ለማውጠንንና ለማስታወስ ተልዕኮ የተሰጠው የአዕምሮ ክፍል አንጎል(አንጎለ አምህርት) ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በንግግርና ጽሕፍት ተግባቦታችን ‘ልብ’ የተባለውን አካል እንጠቀማለን። ‘ልብ ማለት’ ምን ማለት ነው? ለሚለው የአማርኛ መዘገበ ቃላት “ዐሰበ ፣አስታወሰ፣ አጤነ” ይሉታል። ወይንም ‘የተዘነጋውን ነገር ዐሰበ፣ አስታወሰ፣ ነገሩን ለማግኘት ልቡን በዚያ ላይ ጣለ፣ መርምሮ አስተዋለ’ በማለት ትንታኔ ይሰጡታል። የሕግ ታራሚዎች ታዲያ ‘ልብ ይበሉ’ ማለታቸው ለምን ይሆን? ‘ክስተቶችችን/ነገሮችን በአጽንኦት አስቡ፤ አጢኑ፤ አስታውሱ፤ ሰከን ተብሎ ካልታሰበና ካልተወሰነ መዘዙ የከፋ ነው፤ ወንጀል ከመፈጸማችን በፊት ለሚደርስብን ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውስ ቀድመን ከልባችን እናስብ’ ማለታቸው ይሆን?

በአጠቃላይ በማረሚያ ቤቱ ጥቅሶች ከሌሎች (ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ግድግዳዎች) ከሚገኙት ጽሁፎች ጋር ጭብጣቸው ይለያል። እንደ መሰናበቻ ግን የአንድ ታራሚ ስለጥቅሶች ያለኝን ላንሳ። በሸማ ስራ ላይ ያገኘሁት ይገረም አሰፋ(ታራሚ) ሸማ ከሚወረውርበት ወንበሩ ጀርባ ግድግዳው ላይ ሰፋ ያለ ካርቶን አንጠልጥሏል። ከካርቶኑ ላይ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ስዕላት አሉ(የድንግል ማርያምና የኢየሱስ ክርስቶስ)፤ ጽሁፎችም አሉ። እኔም ስለግድግዳ ላይ ጽሁፎች ይገረምን ጠየኩት። መልሱም አንዲህ አለ!

“ውጭ ላይ ብዙ ሰው የማይወደቸውን ነገሮች አድርጌ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን በእነዚያ ነገሮች ተጸጽቻለሁ። በአስታሳስብም በሙያም ተለውጫለሁ፤ በቂ ክህሎት አግኝቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ውጭ ላይ ጊዜ አግኝተህ የማትጽፋቸውን ነገሮች ከዚህ ግን ትጽፋለህ። ለምሳሌ ይሄ ‘ሰውን ውደድ እንጂ አትመን’ ነው የሚለው” አለኝ።

ከይገረም ሃሳብ በመነሳት ታራሚዎች ውጭ ላይ ሆነው የማይጽፉትን ጉዳይ በማረሚያ ቤት ግድግዳ ላይ ከጻፉ ጽሁፎቹ ‘ታራሚ ጥቅሶች’ ላለመባል ምን ያንሳቸዋል?