ማእከሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አሰልጥኖ ወደስራ ሊያሰማራ ነው

53

ሚያዝያ 8/2011 የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ በማሰልጠን ወደ ስራ ለማስገባት የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መስጠት መጀመሩን ገለጸ።

በስልጠናው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 50 ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ሲሆኑ ማዕከሉ ስልጠናውን የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተባበር ነው።

በምግብ ዝግጅት፣ በሆቴል መስተንግዶና በሆቴል አያያዝ ለ15 ቀናት ስልጠና የሚያገኙት ሴቶቹ ከስልጠናው በኋላ ወደስራ እንደሚገቡ ታውቋል።

ማዕከሉ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን አሰልጥኖ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ በመፍጠሩ አገራዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገልጸዋል።

በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችም በሙያው የሰለጠኑ ሴቶችን በመቅጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ዲን አቶ ግሩም ግርማ እንደገለጹት ስልጠናው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ያደርጋል።

በተጠቃሚዎች ፍላጎት መሰጠት የጀመረው ይህ ስልጠና በቀጣይም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለአደጋ ተጋላጭ ሴቶች ተመሳሳይ ስልጠና በመስጠት ወደስራ እንዲገቡ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያለው የባለሙያ ቁጥር ውስን መሆን በዘርፉ ሰፊ የሆነ የስራ ዕድል በመኖሩ አጋጣሚውን በመጠቀም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራት እንደሚገባውም አመልክተዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የሆኑት መስከረም ግርማ እና ሙሪዳ መሐመድ እንደገለጹት ያሉበትን ህይወት የሚቀይር አጋጣሚ አድርገው በመውሰድ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ባገኙት ዕድል ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም