ሆስፒታሉ 15 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የሕክምና መሳሪያዎችን በድጋፍ አገኘ

57

ሚያዝያ  8/2011 የአክሱም ቅድስት ማርያም ጠቅላላ ሆስፒታል 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችን በድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

ሆሰፒታሉ የቁሳቁስ ድጋፉን ያገኘው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሆኑን ገልጿል ።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል ወልደገብሪኤል ለኢዜአ እንደገለፁት ሆስፒታሉ የተደረገለት የቁሳቁስ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያስችለዋል ።

"ሆስፒታሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተገልጋይ የሚያስተናግድ በመሆኑ የነበረበትን የህክምና መሳሪያ እጥረት ለማቃለል በሚኒስቴሩ በኩል ድጋፍ ተደርጎለታል" ብለዋል ።

ሚኒስቴሩ ለሆስፒታሉ በድጋፍ የሰጠው የራጅ ማንሻ፣ የቀዶ ህክምና መስጫ፣ የጨቅላ ህጻናት ማ ቆያ ማሽኖችን ጨምሮ 34 ዓይነት የህክምና መስጫ መሳሪያዎችን ነው።

እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ሆስፒታሉ በ27 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ የህክምና መስጫ ክፍሎች እያስገነባ ነው ።

በሆስፒታሉ የህጻናት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ብርሃኑ ወልዱ በበኩላቸው በድጋፍ ከተገኙ መሳሪያዎች መካከል አብዛኞቹ ለህጻናትና እናቶች ህክምና አገልግሎት መስጫ የሚያገለግሉ ናቸው ።

"ድጋፉ በዘርፉ የነበረውን የህክምና መስጫ መሳሪያ እጥረት በማቃለል የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ለማጠናከር ያስችላል"ብለዋል ።

በተለይ ከክብደት በታች ለሚወለዱ ህጻናት እንክብካቤ ማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን በድጋፍ መገኘቱ በሆስፒታሉ የእቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል ።

ሆስፒታሉ  በዓመት በአማካኝ ለ200 ሺህ ታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም