የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎት ለማግኘት የህግ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል....አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ

130

ባህር ዳር  ሚያዚያ 8 / 2011 የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎት ለማግኘት የህግ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ሲሉ የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጠየቁ፡፡

የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎት ለማግኘት የህግ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ሲሉ የጥረት  ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጠየቁ፡፡

በክልሉ ጠቅላይ ፈርድ ቤት 3ኛ ምድብ ችሎት ዛሬ በቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበውን ክስ ለማዳመጥ ችሎቱ ለሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ክሱን በማዳመጥ የእምነት ክህደታቸውን ለመስጠት ዛሬ ችሎት የቀረቡት አቶ በረከት ስምኦን በጠበቆቻቸው ላይ በሚደርስ ዛቻና ማስፈራሪያ ተገቢውን የህግ አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የተፋጠነ ፍትህ ለማግኘት ከህግ ባለሙያዎች በፕላዝማ የተደገፈ ሙያዊ ድጋፍ  እንዲያገኙ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

የክስ ፋይሉ ትናንት ማምሻው ላይ እንደደረሳቸውና ጉዳዩን በዝርዝር ለማየትና ከህግ  ባለሙያ ጋር ለመመካከር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፡፡

"የክስ መዝገቡ 1 ሺህ ዘጠኝ ገጽ አሉት" ያሉት አቶ በረከት ይህን አገላብጦ ለማየትና ከህግ ጋር ለማገናኘት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ታዳሰ ካሳ በበኩላቸው የፕላዝማ ችሎቱ  የማይፈቀድበት ሁኔታ ካለ የተለየ የህግ ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በበኩሉ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ጊዜ እንዲሰጣቸው ያቀረቡትን አቤቱታ እንደማይቃወም አስተያየቱን  ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም በጉዳያቸው ላይ የፈለጉትን ጠበቃ አቅርበው እንዲከራከሩ መንግስት ለጠበቆቻቸው ልዩ ጥበቃ እንዲደረግ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም ጠይቋል፡፡

የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች በህግ አማካሪ የመከራከር ህገ  መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርና በጠበቆቻቸው ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለማስቀረት የክልሉ መንግስት ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ህይ የማይተገበር ከሆነ በቀጣይ ተጠርጣሪዎቹ የህግ ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚመቻች አስታውቋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የቀረበውን የክስ መዝገብ መርምረውና ከባለሙያ ጋር ተመካክረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት እንዲችሉ የጠየቁትን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ  ለሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም