የኢትዮጵያና ቱርክ ፓርላማዎች የሁለቱ አገሮች የልማት ትብበር እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ይደረጋል

4243

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2010 በኢትዮጵያና ቱርክ ፓርላማዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በሁለቱ አገሮች የልማት ትብበር ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እንደሚደረግ የኢትዮጵያና ቱርክ የወዳጅነት ኮሚቴ አስታወቀ።

የኢትዮጵያና ቱርክ የወዳጅነት ኮሚቴ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከርን ዓላማው አድርጎ እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ የኮሚቴው ሊቀመንበር ሃሰን ሰርት የተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ለመምከር አዲስ አበባ ይገኛሉ።

እስካሁን ባለው ሂደት ከኮንስትራክሽ ሚኒስትር ወይዘሮ አይሻ መሃመድ ጋር ሁለቱ አገሮች በዘርፉ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኮሚቴውን ሊቀመንበር ዛሬ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይታቸው በዋናነት የኢትዮጵያና ቱርክ ፓርላማዎች በሁለቱ አገሮች የልማት ትብብር ላይ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት እንዳሉት፤ ፓርላማዎቹ በአገሮቹ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ የሚኖራቸውን ሚና በሚመለከት ሊቀመንበሩ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ጋር ተወያይተዋል።

የቱርክ ፓርላማ አባላት ትብብሩ እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ መግለጻቸውን የኮሚቴው ሊቀመንበር ለፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ኮሚቴው የሁለቱ አገሮችን ፓርላማ ግንኙነት ለማጠናከር እያከናወነ ያለውን ተግባር ማድነቃቸውን የተናገሩት አቶ አሸብር፤ መንግስት ለኮሚቴው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤ ሊቀመንበሩ በቀጣይ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ጋር ይወያያሉ።

በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ እ.አ.አ በሃምሌ 2017 ባወጣው መረጃ 165 የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን አውጥተው እየሰሩ መሆኑንና በሁለቱ አገሮች መካካል ያለው የንግድ ልውውጥ 440 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አመላክቷል።