ኢንስቲትዩቱ ከግዥ ጋር ተያይዞ የሚታዩበትን የአሰራር ክፍተቶች ማስተካከል አለበት ተባለ

42

አዲስ አበባ ሚያዚያ 8/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከግዥ ጋር በተያያዘ የሚታዩበትን የአሰራር ክፍተቶች ማስተካከል እንዳለበት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ለዘርፉ አጋዥ የሆኑ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያደረገ ቢሆንም ከሙከራ ባለፈ ወደ ተግባር መግባት አልቻለም ተብሏል።

በምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትን የስራ ክንውን የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ቋሚ ኮሚቴው ከኢንስቲትዩቱ ሰራተኞችና አመራሮች ጋር ተወያይቷል፤ በመስሪያ ቤቱ የሚከናወኑ ስራዎችንም ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

ከምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴው አባል መካከል አቶ ዲጊሶ ጎና እንዳሉት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማዘመን ኢንስቲትዩቱ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ አለበት።

ዘርፉ ብዙ ተዋንያን ያሉበት በመሆኑ በግዥ ሂደቱ ላይ ግልጽነትና ተጠያቄነት በሰፈነበት መንገድ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል።

"በኢንስቲትዩቱ በተጋነነ የዋጋ ተመን እቃዎች ተገዝተው እንደሚገቡ ከሰራተኞች ጋረ ባደረግነው ውይይት ማረጋገጥ ችለናል" ያሉት አቶ ዶጊሶ ይህ የተጋነነ የጨረታ ግዥ የመንግስትን ሃብት ማባከን ስለሆነ መቆም አለበት ብለዋል።

ለአብነት አንድ ኮምፒውተር 185 ሺህ ብር ወጭ ተገዝቶ መግባቱንና በወቅቱ ትክክል አይደለም ብለው ቢናገሩም አመራሮቹ ምላሽ አለመስጠታቸውን ከሰራተኞች ሰምተናል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአመራሮችና ባለሙያዎች በመካከላቸው ያለው የመረጃ ልውውጥ ተቀራርበው መስራትና የኮንስትራከሽን ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አስመሮም ታደሰ በበኩላቸው ከግዥ ጋር በተያያዘ የቀረበው አስተያየት ትክክለኛ የነበረና ነገር ግን በወቅቱ ተጣርቶ ምላሽ እንደተሰጠበት ገልጸዋል።

"በኢንስቲትዩቱ እየተንከባለለ ለመጣው ችግር እኛው በመስሪያ ቤቱ የተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የነበርን በመሆኑ በማንም አናሳብብም ሃላፊነቱን እንወስዳለንም" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠንን ግብረ መልስ ሙሉ በሙሉ በመውሰድ የቀጣይ የስራችን አካል እናደርገዋለን፣ ከሰራተኞቹ ጋር የመረጃ ክፍተት እንዳለብን አይተናል ይሄንንም እናስተካክላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም