በደብረ ብርሃን ከተማ መሰረተ ልማት ሥራዎች ፈጥነው ስለማይጠናቀቁ ለሀብት ብክነት እየተጋለጡ ነው....ነዋሪዎች

153

በደብረ ብርሃን ሚያዝያ 7/2011በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በተያዘላቸዉ የጊዜ ገደብ ስለማይጠናቀቁ ለሀብት ብክነት እየተጋለጡ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ጌጤ ታምሩ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው በየዓመቱ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል፡፡

የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በሚመለከተው አካል ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑንም ተቁመዋል።

"የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ ቀደም ብሎ ተገቢው ዝግጅት ተደርጎባቸው አይጀመሩም" ያሉት ነዋሪዋ በተለይ የመንገድ፣ የድልድያና የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ንጣፍ ስራዎች በዓመቱ ማለቂ ላይ  የሚጀመሩበት ሁኔታ ማስተዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ከክረምት መግባት ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት መጓደል ምክንያት ለብልሽት ሲዳረጉና የህዝብና የመንግስት ሃብት ሲባክን ማየታቸውን ተናግረዋል።

በከተማው ቀበሌ 04 እና 05 ለማገናኘት በ2009 መጋቢት ወር ላይ የተጀመረው የድልድይ ሥራ በ2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ድረስ አለመጠናቀቁን በማሳያነት አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት የጀመራቸዉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በአብዛኛዉ ከመጋቢት አጋማሽ ወድህ የተጀመሩ በመሆናቸዉ በውሉ መሰረት ይጠናቀቃሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

"በከተማው ከመገንጠያ እስከ ብርድልብስ ፋብሪካ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ ግንባታ ዘግይቶ በመጀመሩ በአሁን ወቅት በአካባቢው እየጣለ ባለው ዝናብ ምክንያት እየተጓተተና  ለጥራት ችግር የተጋለጠ ነው" ሲሉም ጠቁመዋልል፡፡

"መንግስት ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብም እስካሁን ድረስ አልተፈታም" ብለዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ ዶክተር ተክለ በየነ በበኩላቸዉ ከዚህ በፊት በቀሌ 03 እና 06 የተገነቡ መንገዶች ከፍተኛ ወጪ ቢወጣባቸዉም በጥራት ችግር ፈጥነዉ ለብልሽት መዳረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

"አብዛኞቹ የልማትስራዎች ለተቋራጭ የሚሰጡት ከዓመቱ አጋማሽ በኋላ በመሆኑ ከክረምት መግባት ጋር በተያያዘ ለግንባታ መጓተትና ለጥራት ችግር እየተጋለጡ ነው" ብለዋል፡፡

የሀብት ብክነትን ለመከላከልካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመውሰድ የመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ ስራዎች በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በሚገኙ ወራት ስራቸው እንዲጀመር ቢደረግ መልካም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪጅ አቶ መኮንን አስፋዉ በበኩላቸው በከተማው በዚህ ዓመት በ100 ሚሊዮን ብር 31 የልማት ፕሮጀከቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሚሰሩት የልማት ሥራዎች መካከልም የአስፓልት ፣ የጌጠኛ ድንጋይና የጠጠር መንገድ ግንባታዎች እንዲሁም የተፋሰስ ስራ፣ የወጣቶች ማዕከል ግንባታ፣ የመብራትና የንፁህ የመጠጥ ውሃ መስመር ዝርጋታዎች ይገኙበታል፡፡

ለመሰረተ ልማትስራዎች በጀት ፈጥኖ አለመለቀቅና የጨረታ ሂደት መጓተት ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ይህን ለማስተካከል እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመት የተጀመሩ የልማትሥራዎች በተገባው ውል መሰረት እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቀቁ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ ከ1 ሺህ 500 ለሚበልጡ የከተማው ነዋሪዎችም የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸው ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም