ኤጀንሲው የሚሰጠውን የደረጃዎች ምልክት ተቋማት በትክክለኛው መንገድ መጠቀማቸውን መከታታል አለበት

67

አዲስ አበባ ሚያዝያ 07/2011የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ የሚሰጠውን የደረጃዎች ምልክት ተቋማት በትክክለኛው መንገድ መጠቀማቸውን የመከታታል ስራ መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የ2011 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዛሬው እለት አድምጧል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ምርቶች ላይ የሚደረጉ ምልክቶች የትም የሚታተሙና ሐሰተኛ ምርቶችን ለማምረት የተጋለጡ ናቸው።

ይህም በቴክኖሎጂ ተደግፎ የደረጃዎቹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ከባድ እንደሆነ ጠቅሰው በመሆኑም ኤጀንሲው የሚሰጠው የደረጃዎች ምልክት በህግና በትክክለኛው መንገድ መተግበር አለመተግበራቸውን የመከታታል ስራም መስራት ይኖርበታል።

በቀጣይም በኤጀንሲው የሚሰጡ ደረጃዎች በቴክኖሎጂ ንባብ በቀላሉ ህብረተሰቡ እንዲለያቸው የማድረግ ሥራ መሰራት አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ደረጃዎችን ለይቶ በማዘጋጀት በኩል በርካታ አበረታች ስራዎችን እየሰራ ሲሆን የሚዘጋጁት ደረጃዎች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ደረጃዎቹን የማጽደቅ ሥራ መስራት አለበት ብለዋል።

አስገዳጅ ደረጃዎች ተብለው በኤጀንሲው የተለዩት 20 የሚሆኑ ደረጃዎች ህብረተሰቡ እንዲያውቋቸው የማድረግ ተግባራትንም መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅሞ ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ይህም ህብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ ብቻ ሳይሆን ደህንነቱ የተመሰከረለት ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችለዋል ሲሉም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ግብረ መልስ እንደ ግብዓት ተጠቅመው የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።

ተቋሙ በስልጠና፣ በግልጸኝነትና ተጠያቂነት፣ በስነ ምግባርና በሙስና፣ በቅሬታ አቀራረብና አፈታት፣ በተገልጋይ እርካታ፣ከሴቶች ተጠቃሚነት፣ ሰራተኞችን በትምህርት ከማብቃትና ደረጃዎችን ለይቶ ከማዘጋጀት አንጻር አቅዶ ሲሰራ እንደነበርም ገልጸዋል።

በዚህም ከአጠቃለይ የእቅዱን 88 በመቶ ማስፈፀም መቻሉን ጠቁመው በቀጣይም ተለይተው የተዘጋጁትን ደረጃዎች የማፀደቅ ስራ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በ800 የደረጃዎችና በ240 የደረጃ ምልክት አተገባበር ላይ ክትትል የተደረገ ሲሆን 20 አስገዳጅ ደረጃዎች ተለይተው እየተሰራባቸው ይገኛልም ብለዋል።

አስገዳጅ ደረጃዎቹን በበራሪ ጽሁፎች፣በባዛሮችና በኢግዚቢሽኖች፣ ለማስዋወቅም እየተራ ሲሆን በመገናኛ ብዙሃን ለማስተዋወቅ ግን የበጀት እጥራት መኖሩን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም