በፓርኩ የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር እስከሚውል ድጋፉን እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኢምባሲ አስታወቀ

87

ጎንደር ሚያዝያ 6/2011 በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ሚስተር ኦር ዳንኤል አስታወቁ፡፡

በእሳት አደጋ ቁጥጥር ስራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የእስራኤል ባለሙያዎች በፓርኩ የተከሰተውን ቃጠሉ ለመከላከል ዛሬ ስራ ጀምረዋል፡፡

በስፋራው የተገኙት ምክትል አምባሳደሩ እንደገለጹት ባለሙያዎቹ የመጡት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኩል ለእስራኤል አቻቸው በስልክ በተጠየቀው የትብብር ድጋፍ መሰረት ነው፡፡

" ኢትዮጵያና እስራኤል የጠበቀ የጥንት ግንኙነት ያላቸው ናቸው፤  ይህ የድጋፍ ስራ የአለም የቅርስ ሀብት የሆነውን ከመታደግ ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል" ብለዋል፡፡ 

የእሳት ቃጠሎው  አሁን ባለበት የፓርኩ ክፍል ልዩ ስሙ ግጭ እና ሙጫሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በመድረስም ምልከታ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ፡

በፓርኩ የደረሰው ጉዳት እንዳሳዘናቸው ገልፀው የእሳት አደጋ  በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ባለሙያዎቹ የሚሰጡትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው ከፍተኛ አመራሩ፣ የአካባቢው ህዝብ በተለይም ወጣቱና የፓርኩ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች እንዲሁም የፀጥታ አካላት ከእስራኤላዊያን  ጎን ሆነው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ከኬኒያ በትብብር የመጣው  ሄሊኮፕተር ከፓርኩ በቅርብ ርቀት በሚገኝ አሰራ ተብሎ በሚጠራ ወንዝ አስፈላጊውን ውሃ እያገኘ እሳት ቃጠሎውን  ለመቆጣጠር የማጥፋት ስራውን መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም