የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅና አማካሪያቸው ኢቫንካ ትራምፕ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

377

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011  የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅና አማካሪያቸው ኢቫንካ ትራምፕ ለሁለት ቀናት ስራ ጉብኘት አዲስ አበባ ገቡ።

ኢቫንካ ትራምፕ ጉብኝት በዋናነት በአፍሪካ የሴቶች ምጣኔ ሀብት አካታችነትና አሳታፊነት ላይ በሚያጠነጥነው ጉባኤ ለመሳተፍ ነው ተብሏል።

ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በአፍሪካ ሕብረት የአሜሪካ አምባሳደር ሜሪ ቤት ሌዮናርድ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነርና ሌሎች የአሜሪካ በቀል ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጉብኝቱ አሜሪካ በቀል  የሴቶችን ተሳትፎ ለማበረታታትና  የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ጥረቶችን ለማሳደግ ማለሙን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲና ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች እንዲመጡ አጋርነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑንና ለ2063 የአፍሪካ የልማት ግቦች ስኬት ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ ቡና ቀመሳ ስነ ስርዓት ጉብኝታቸውን የጀመሩት ኢቫንካ ትራምፕ፣ ከሴት ስራ ፈጣሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ቆይታቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና የንግዱ ዓለምና የሲቪክ ማኅበራትን ሴት መራሂታት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ጠበቃል። 

ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኋላ ለተመሳሳይ ሁለት ቀናት ጉብኝት ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮትድቮር ያመራሉ ተብሏል።