አብሮ የመኖር እሴት በማስቀጠል ህዝቡ ለአገር ሠላም በጋራ እንዲሰራ ጥሪ ቀረበ

62

አዲስ አበባ ሚያዝያ 6/2011 ለዘመናት የተገነባውን አብሮ የመኖር ኢትዮጵያዊ እሴት በማስቀጠል ህዝቡ ለአገር ሠላም በጋራ እንዲሰራ ጥሪ ቀረበ።

''ዘረኝነትን እጸየፋለሁ፤አካባቢዬን አጸዳለሁ'' በሚል መሪ ሀሳብ በመላ አገሪቷ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።  

በአዲስ አበባም መርሃ ግብሩ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች ነዋሪዎችን አሳትፎ ተከናውኗል።

ጽዳቱ ከተካሄደባቸው አከባቢዎችም የልደታ አደባባይ አንዱ ሲሆን ከነዋሪዎች በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ተካፍለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜሞክራሲ ግንባታ ማስተባባሪ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ እንዳሉት፤የዘመቻው ዓላማ አዲስ አበባን እንደስሟ ፅዱ ከማድረግ ጎን ለጎን ፈተና እየሆነ የመጣውን የዘረኝነት አስተሳሰብ ለማንፃት ነው።

የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ወደ ፊት እንዲሄድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጽዳቱ ተሳታፊዎች በአገሪቷ አብሮነትን የሚሸረሽሩ ትርክቶች እንዲወገዱ አበክሮ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅርን፣አንድነትና መተሰሳሰብን ለማውረስ ግዴታቸውን እንዲወጡ ይገባል ባይ ናቸው።

ወይዘሮ አስቴር አበራ በሰጡን አስተያየት ዕዳት የሁል ግዜ ተግባር ቢሆንም ዛሬ ከህሊና ጽዳት ጋር ተሳስሮ እንድንሳተፉ መደረጉ ደስታን ፈጥሮብኛል ብለዋል።   

ጥላቻን ለማስወገድ የጥላቻ መሰረት የሆኑትን ወሬዎች በማስተማር በተለይ ትውልድ እንዲለወጥ መሥራት እንደሚገባም አዕንኦት ሰጥተዋል።

"ጽዳቱ መጀመር ያለበት ከጭንቅላት ነው" በማለት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑት የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ጤናወርቅ ጉልማ ናቸው

ዘረኝነት እንዲባበስ ከሚያደርጉ መንስኤዎች መካከል የባለስልጣናት አድሏዊ አሰራር መሆኑን የተነገሩት አቶ ፍሬው በቀለ ''ሀኪም በሰብአዊነት ሁሉንም በእኩል እንደሚያገለግል ሁሉ ባለስልጣናትም ዜጎችን በፍታዊነት ማገልገል አለባቸው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም