ማህበሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን ካስጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ከፊሎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን ካስጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ከፊሎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት በቁ
አምቦ ግንቦት 26/2010 በኦሮሚያ ልማት ማህበር የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 15 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ካስጀመራቸው 12 የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ከፊሎቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ መረራ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አራት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ይገኙበታል። ከእዚህ በተጨማሪ ሁለት የእንስሳት ጤና ኬላና አንድ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከልም ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል። ማህበሩ የልማት ሥራዎቹ ያካሄደው አምቦ ከተማን ጨምሮ በቶኬ ኩታዬና ጅባት ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል። ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ ፕሮጀክቶች ማህበሩ አምናና ዘንድሮ ካስጀመራቸው 12 የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ከሚገኙት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የደንዲ አንደኛ ደረጃና የዳኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ሥራዎች ይገኙበታል። የአቡና ግንደበረት እና ሜታሮቢ ወረዳዎች የወጣቶች ማዕከላት እንዲሁም በአድአ በርጋና ኢልፈታ ወረዳዎች የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ግንባታ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም ግንባታቸው ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን የጠቀሱት አስተባባሪው፣ "የተጠናቀቁትና በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች ማህበራዊ አገልግሎት ችግር የሚያቃልሉ ናቸው" ብለዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ማህበሩ ከአባላቱ ከሚሰበስበው መዋጮ 90 በመቶ ለአካባቢው ልማት እያዋለ ይገኛል። ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበሩ ባከናወነው እንቅስቃሴም 250 የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለሕብረተሰቡ ማስረከቡ ተመልክቷል። በኖኖ ወረዳ የስልክአምባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ንጉሴ ጉርሜሳ በሰጡት አስተያየት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል በአካባቢው መገንባት የእርሳቸውን ልጆች ጨምሮ የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያቸውን በማይገባ ቦታ ከማሳለፍ እንደሚታደግ ተናግረዋል። ሕብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበሩ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ደግሞ የጅባት ወረዳ ሸነን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙለታ ዱጋሳ ናቸው፡፡ "ማህበሩ በአካባቢያቸው የሰራው የውሃ ተቋም የመጠጥ ውሃ ችግራችንን አቃሏል" ያሉት ደግሞ በአምቦ ወረዳ የወዴሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሪጊቱ ጫላ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ልማት ማህበር በዞኑ ከሚገኙ 336 ሺህ 342 አባላቱ ዘንድሮ እስከ ሦስተኛው ሩብ በጀት ዓመት 9 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።