ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳቶቿን ልታጣቸው ትችላለች ተባለ

309

አዲስ አበባ  ሚያዝያ6/2011  በኢትዮጵያ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ በመምጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካቶቹን ጨርሶ ልታጣቸው እንደምትችል የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የዱር እንስሳት በተፈጥሮ በታደሉትና ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ ጫካ፣ ደን፣ ቁጥቋጦ፣ ሜዳማና ተራራማ ሥፍራ አሊያም በተራሮችና በውኃማ አካባቢች ይኖራሉ።

እንስሳቱ ለሰው ልጅ የምግብ ምንጭ ከመሆን ባሻገር የምድርን ለምነት ለመጠበቅና ዕፅዋቱም ከምግብ ምንጭነታቸው ባለፈ የባህላዊ መድኃኒቶች በመሆን ብሎም ለሰው ልጆች የሚተነፍሱትን ንፁህ አየር (ኦክስጅን) በመለገስ የማይተካ ድርሻ እንደሚያበረክቱ እሙን ነው።

በዚህም ረገድ በዓለም ላይ ልዩና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች ከሚገኙባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይጠቀሳል።

በአስገራሚ የተፈጥሮ መሬት አቀማመጧም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም ጭምር ምቹ በመሆኗ ስመ ጥር እንደሆነችም ይነገርላታል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተለይ ብርቅዬና ዋና ዋና በሆኑት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት በተለያየ መልኩ ቁጥራቸው እየተመናመነና እየጠፉ መምጣታቸው አሳሳቢ ሆኗል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቷል።

በተለይ ለግጦሽ ፣ ለእርሻ፣ ለሰፈራና ለሌሎችም ተግባራት የህዝቡ የመሬት ፍላጎት መጨመርና በመንግስትም በኩል ኢኮኖሚውን ከማሳደግ አንጻር ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሲባል የመሬት ፍላጎት ሰፊ መሆኑ ለእንስሳቱ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርላቸው ምክንያት ሆኗል።

በተለይ ቀይ ቀበሮ፣ የዱር አህያ፣ ዜብራ፣ ዝሆን፣ አንበሳ፣ አቦሸማኔ፣ቀጭኔ እና ሌሎችም ብርቅዬ እንስሳቶቿ ቁጥራቸው በእጅጉ እየተመናመነ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውሰጥ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳቶቿን ጭራሽ ልታጣ እንደምትችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ይህም መሆኑ በአገር ገጽታና በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩ የሁሉም መሆኑን በመረዳት መንግስትና ህዝቡ ከባለስልጣኑ ጎን በመቆም ለእንስሳቱ አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ትናንሽ አጥቢ እንስሳቶችንና አእዋፋትን ጨምሮ 50 አይነት ብርቅዬ የዱር እንስሳት ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል ዋልያ 1 ሺህ የሚጠጋ፣ የስዌይን ቆርኬ 800፣ ዝሆን 2 ሺህ የሚሆን እንዲሁም አንበሳ 1 ሺህ የሚደርሱ እንደሚገኙ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም