ህብረተሰቡ አካባቢውን ከማፅዳት በተጓዳኝ የጥላቻ አስተሳሰብን ለማስወገድ መተባባር አለበት--- ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ

122

አዳማ  ሚያዝያ  6/2011 ህብረተሰቡ አካባቢውን ከማፅዳት ጎን ለጎን የጥላቻ አስተሳሰብና ንግግሮችን ለማስወገድ ጭምር መተባበር እንዳለበት  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ አሳሰቡ።

" አካባቢያችንን በማፅዳት የጥላቻ አመለካከትን እናስወግድ"  በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ  በአዳማ ከተማ የፅዳት ዘመቻ ተጀምሯል።

የክልሉ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ፕሮግራሙን ባስጀመሩበት ወቅት " በአካባቢያችን ያለውን ቆሻሻ ከማፅዳት ጎን ለጎን በጥላቻ የቆሻሸውን አእምሮ ማፅዳት ይገባናል "ብለዋል።

"ቆሻሻ አካባቢን ይበክላል ያበላሻል"  ያሉት  ፕሬዝዳንቱ የጥላቻ ንግግር አስተሳሰብና አመለካከት የህዝቦችን መከባበርና መቻቻልን በመሸርሸር ለጥፋትና ውድመት እንደሚዳረግ ተናግረዋል፡፡

"የኦሮሞ ህዝብም ሆነ በክልሉ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት አዳማ ከተማንም ሆነ ክልሉን ከቆሻሻ ለማፅዳት የጀመሩትን ዘመቻ ጎታች አስተሳሰብና አፍራሽ ድርጊቶችን በማስወገድ ጭምር መድገም ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል።

ህዝቡ አሁን እየታየ ያለውን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች በመታገል የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ግቡን እንዲመታ በአንድነት መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

መላው የክልሉ ወጣቶችና  ቄሮዎች የተገኘውን የፖለቲካ ድሉን  በልማት ፣በሰላምና በመልካም አስተዳደር ለመድገም በቅንጅት እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል።

መልካም አስተሳሰብን ለመስበክ የሚያግዝ የጽዳት ዘመቻ ዛሬ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ብለው ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

" ዘረኝነት ቆሻሻ ነው፤ እናቃጥለው፤ እንቅበረው"  በሚል መልዕክትን ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት በማሳማት ነው ስራው የሚካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም