ማህበሩ የጦር ጉዳተኛ አባላቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

71

መቀሌ ሚያዝያ 5/2011 የትግራይ የጦር አካል ጉዳተኞች ማህበር ከ13 ሺህ በላይ አባላቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ  የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ተግባራዊ እንደሚያደረግ አስታወቀ።

ማህበሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ  ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ይጠይቃል።

በጀቱ የሚሸፈነው ከማህበሩ የውስጥ ገቢ፣ ከትግራይ መልሶ ማቋቋም ተቋም ፣ከተለያዩ ምግብረሰናይ ድርጅቶችና በውጭ ከሚኖሩ የክልሉ ልማት ደጋፊዎች  በሚሰበሰብ ገንዘብ  መሆኑን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጨርቆስ ወልደማርያም  በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

"ከማህበሩ አባላት መካከል  ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው  2ሺህ 552 ሴት ታጋዮች በገጠርና በከተማ በንግድና በገጠር ልማት ስራዎች እንዲሰማሩ ይደረጋል" ብለዋል ።

በአነስተኛ ንግድ፣ በእንስሳት ሃብትና በጓሮ አትክልት ልማት ስራዎች ለሚሰማሩ አባላት በነብስ ወከፍ 40 ሺህ ብር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል ።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ እንዳሉት ከባድ የአካል ጉዳት ደረሶባቸው መንቀሳቀስ ለማይችሉ ታጋዮች ከተያዘው ወር ጀምሮ በየወሩ 2ሺህ ብር ድጎማ ይደረግላቸዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት የአካል ጉዳተኛ ታጋይ  የሻረግ መዓርግ በሰጡት አስተያየት ወርሀዊ የድጎማ ገንዘብ እንዲያገኙ በመታሰቡ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

"በክልሉ በገጠር የሚገኙ የጦር ጉዳተኛ ታጋዮችም ባሉበት ተመሳሳይ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል" ብለዋል ።

በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በአነስተኛ ንገድ ስራ ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን  የገለጹት  ደግሞ የጦር ጉዳተኛ ታጋይ መረሳ  አበራ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም