የክልሉ ጋዜጠኞች እገዛ ጠየቁ

67

አሶሳ ሚያዝያ 5/2011 ህብረተሰቡን በማገልገል ኃላፊነታውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት የክልሉ መንግስት ተገቢውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች ጠየቁ፡፡

የአሶሳ ኤፍ ኤም 91.4 ሬዲዮ ጣቢያ ዛሬ ተመርቋል፡፡

ከድርጅቱ ጋዜጠኞች መካከል አቶ አፈወርቅ ጥላሁን በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገረው ድርጅቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢኖረውም በተደራጁ የባለሙያዎች ቡድን እየተመራ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

አንዳንዴ በሙያው ያልበቁ በአዘጋጅነት በተቋሙ አመራነት እንደሚመደቡ አመልክቶ  የተቋሙ ግቢ ተገቢው ጥበቃ እንደማይደረግለት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር  በአሶሳ ከተማ የተፈጠረው  የጸጥታ ችግር ወቅት የሬዲዮ ጣቢያው ስርጭት  ተስተጓጉሎ እንደነበር  በማስታወስ ጠቅሷል፡፡

ጋዜጠኛ ደስታ አበበ በበኩሏ  " በተለይም በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ በሚያዘጋጁት ዜና እና ፕሮግራሞች የአመራሩ ጣልቃ ገብነት አለ " ብላለች፡፡

በባለሙያዎች በኩል ችግሮችን ተጋፍጦ መፍትሄ በማምጣት ለህብረተሰቡ መረጃን በማቅረብ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉ ተናግራለች፡፡

የክልሉ መንግስትም አዲስ የተጀመረውን ሬዲዮ ጣቢያ በሰው ሃይል፣ በቁሳቁስና በበጀት ከማጠናከር ጀምሮ ትኩረት በመስጠት እንዲያግዛቸው  ጋዜጠኞቹ ጠይቀዋል፡፡ 

የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ አብዱላዚዝ ተቋሙ የጋዜጠኝነትን የሙያ ስነ-ምግባር በተላበሰ መልኩ እንደሠራ ጥረት እንደሚያደረግ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት ባደረጉት ንግግር መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በመቅረጽ በተለይም እንደኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ወሳኝ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

" በክልሉ የሚገኘው መገናኛ ብዙሃን በበጀት እጥረት ምክንያት በሚፈለገው ልክ አልተጠናከሩም" ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በቀጣይ በተቋሙ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በቅርብ ክትትል  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ አድጎ አስታውቀዋል፡፡

ባለሙያዎቹ አንገብጋቢ የህዝብ አጀንዳዎችን ከማንሳት ጀምሮ የአካባቢውን ባህል እና የተፈጥሮ ሃብት በማስተዋወቅ ሚናቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት የጀመረው የአሶሳ ኤፍ ኤም 91.4 ሬዲዮ ጣቢያ በክልሉ ለሚገኙ 20 ወረዳዎች ተደራሽ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ የክልሉን ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሮ የሚውል ባለሶስት ፎቅ ህንጻ ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ከአማርኛ በተጨማሪ በበርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሽኛ፣ ማኦ እና ኮሞ ቋንቋዎች የሚሰሩ 63 ጋዜጠኞች አሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም