በምዕራብ ሸዋ ባለሀብቶች ያላለሙት ከ630 ሄክታር በላይ መሬት እንዲመልሱ ተደረገ

76

አምቦ ሚያዝያ 5/2011 ባለሀብቶች  ወስደው ያላለሙት ከ630 ሄክታር በላይ መሬት እንዲመልሱ መደረጉን  የምዕራብ ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

መሬቱ ሊመለስ የቻለው ባለሀብቶች በውላቸው መሰረት ባለማልማታቸው ነው።

በጽህፈት ቤቱ የኢንቨስትመት ፕሮጀክት ውጤታማነት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሰለሞን ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት ባለሀብቶቹ በውላቸው መሰረት እንዲያለሙ ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡

ማስጠንቀቂያም ተሰጥቷቸው ወደ ልማት ባለመግባታቸው እርምጃው መወሰዱን አስረድተዋል።

ከሶስት የሀገር ውሰጥ ባለሀብቶች እንዲመለስ  የተደረገው ይሄው መሬት  በዞኑ በዳኖ፣ ቶኬ ኩታዬና አምቦ ወረዳዎች ውስጥ የደን ልማትና የግብርና ስራዎችን ለመስራት ወስደው ለአስር ዓመታት ያህል ያለስራ አጥረው አቆይተዋል፡፡

ከባለሀብቶቹ  ተመላሽ የተደረገውም ወደ መሬት ባንክ ገቢ መሆኑን  አቶ ሰለሞን አመልክተዋል።

በተጨማሪ በቶኬ ኩታዬ ፣አደአ በርጋና ኢሉ ገላን ወረዳዎች ውስጥ 72 ሄክታር መሬት በአግባቡ  አላለሙም የተባሉ  ሶስት ባለሀብቶች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ  ገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ሳህሉ ድርብሳ በበኩላቸው ከባለሀብቶቹ የተመለሰው መሬት ወጣቶችን በማደራጀት ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።

የዳኖ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቢፍቱ ጋዲሳ በአካባቢያቸው  መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች እያለሙበት እንዳልሆነ መታዘባቸውን  ተናግረው  በመንግስት  የወሰደው እርምጃ  እንደሚደግፉ አመልክተዋል፡፡

በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ባሉበት ወረዳ ባለሀብቶች ያለ ልማት መሬት አጥረው ማስቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጸው ደግሞ የአምቦ ወረዳ ነዋሪው  ወጣት በረከት መንግስቱ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ ባላቸው አድራሻ ስለጉዳዩን ለማነጋገር  ሞክራ ማግኘት እንዳልቻለች በመግለጽ ጭምር ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግባለች፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን 42 ባለሃብቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተው በመንቀሳቀስ  ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች  የስራ እድል ተጠቃሚ  ማድረጋቸውን ከኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም