የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ስርዓትና ተቋማት ለተቋቋሙለት ዓላማ መዋል አለባቸው

59

አዲስ አበባ ሚያዚያ5/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ስርዓትና ተቋማትን ለተቋቋሙለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።

"አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ" በሚል ርዕስ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያዘጋጀው የምሁራን ውይይት ትናንት ተካሂዷል። 

ውይይቱ ስርዓትና ተቋማት ምንድን ናቸው፣ የስርዓትና የተቋማት ግንባታ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ዳራ በሚሉና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ምሁራኑ ተወያይተዋል።

ከዚህም ሌላ ምሁራኑ በአገሪቱ የአመለካከትና የስነ ምግባር ቁመና  ከስርዓትና ተቋማት ግንባታ አንጻር ምን ይመስላል፣ ይህንን ለማበልጸግ ምን ይጠበቃል እንዲሁም ስርዓትና ተቋማትን ማጠናከር በተመለከተ አዲሱ መንግስት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ምን እርምጃ ወሰደ፤ ምንስ ይቀረዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

ከተሳታፊ ምሁራኑ መካከል የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት፤ ለውጡን ለማስቀጠል ስርዓትና ተቋማት የተጣለባቸውን ዓላማና ግብ ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆን አለባቸው።

እንዲሁም ስርዓትና ተቋማት በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ እኩልነት፣ ፍትሃዊነት፣ ነጻነትና የህግ የበላይነት በማረጋገጥ ሊሰሩ እንደሚገባም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከጉልበት ልዕልና ወደ ሀሳብ ልዕልና መሸጋገር ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ፈንታ ተቋማት ይህን ማድረግ ከተሳናቸው የትም መድረስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ፈንታ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዕልናን ለማረጋገጥ ስልጣኔን ማስቀደም እንዲሁም የሰው አስተሳሰብ ላይ መስራት ያስፈልጋል።

በስርዓትና በተቋማት ዘንድ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ወደ ውስጡ መመልከት እንዳለበት የጠቆሙት ዶክተር ፈንታ ችግሮችን ወደ ውጭ መግፋት ተገቢነት የለውም ባይ ናቸው። 

ስርዓትና ተቋማት የሚፈለግባቸውን ውጤት ለማምጣት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና አመኔታ ሊኖራቸው እንደሚገባም ዶክተር ፈንታ አመልክተዋል።

ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት "አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ" በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፣ የአቅም ግንባታና የአመራር ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ህይወት አለማየሁ እና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየሱስ መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም