የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጠየቀ

128

መቀሌ ሚያዚያ 5/2011 የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አመርቂ ለውጥ ለማምጣት እንዲረባረቡ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጠየቀ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው የሀገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስና ህገ መንግስታዊ ፌደራላዊ ስርዓቱ በጥብቅ እንዲከበር ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ህወሓት በጽናት ይታገላል ብሏል።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 03/2011 ዓ.ም. ድረስ ሲያካሄድ የቆየውን መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ምክንያት በማድረግ ትናንት ማምሻውን  የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው እንዳመለከተው ፣ባለፉት ስድስት ወራት የድርጅቱ መሰረታዊ ተልእኮ የሆኑትን ልማት፣መልካም አስተዳደር ማንገስ፣ ሰላምን በቀጣይነት የማረጋገጥና የማስፋት ስራዎች ሲተገበሩ ቆይቷል።

በተለይ በክልሉ ህዝብ ያላሳለሰ ጥረትና እንቅስቃሴ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው።

የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ተጀምረው ያሉትን እንቅስቃሴዎች ለማጠናከር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አመርቂ ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እንዲያደርጉ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

የትግራይ ህዝብ ተከማችተው የቆዩ ችግሮች እንዲፈታለትና በፍጥነት ለውጥ እንዲመጣ እያሳየ ላለው የውስጥ ፍላጎት መነሳሳት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴው በሚገባ ይገነዘበዋል ያለው መግለጫው፣እንዲህ አይነት ጥያቄና ግፊት ማድረግ ሊደረግ የሚገባው ጉዳይ ነው ብሏል።

በተለይ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች ከመሬት አስተዳደርና ከመሬት ካሳ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች በፍጥነት ለመፍታት ድርጅቱ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እንደሚያደርግም አረጋግጧል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ችግርና መከራ ለማውጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም  ከሌሎች ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አብሮ አሁንም በጽናት ለመታገል ዝግጁ ነው ብሏል።

ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ብሩህ ተስፋና እድገት ታይቶባት የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በሰላም እጦት ምክንያት ህዝቦቿዋ እየተሰቃዩና እየተፈናቀሉ፣በጠራራ ጸሃይ ህይወታቸውና ንብረታቸውን እያጡ ናቸው ብሏል የድርጅቱ መግለጫ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቦቿዋ ዛሬ ከነገ ምን ይፈጠር ይሆን ብለው በስጋት የሚኖሩባት ፣ተሸማቅቀው የሚያድሩባትና በማንነታቸው እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሯል ያለው የድርጅቱ መግለጫ፣በዚህ አጋጣሚ ለደረሰው የሞት እና የህዝቦች መፈናቀል የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።

ወደ ፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰትም ህወሓት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጽናት እንደሚታገል  አስታውቋል።

"ሃገራችን ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን እጅግ አመርቂና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበችበት፣ ሉአላዊነቷዋን አስከብራ እንድትኖርና በህዝቦች በፍጹም መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ያረጋገጠች ኢትዮጵያ እውን የሆነበት ነው" ያለው የማእከላዊ ኮሚቴው መግለጫ፣የአመርቂ ውጤቱን ሚስጥር በጥልቅ መገመገሙን ገልጿል።

የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በመጨረሻም፣በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ሰላም እና ወንድማማችነት ይበልጥ እንዲጠናከርና ዘላቂ እንዲሆን ህወሓት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም