ኢትዮጵያ የኑዩክለር ቴክኖሎጂን ለልማት መጠቀም የሚያስችላትን ድጋፍ ከሩሲያ ለማግኘት እየሰራች ነው ተባለ

75

አዲስ አበባ ሚዝያ 4/2011 ኢትዮጵያ የኑዩክለር ቴክኖሎጂን ለልማት መጠቀም የሚያስችላትን ድጋፍ ከሩሲያ ለማግኘት እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።     

ሩሲያዊው ዩሪ ጋጋሪ ስፔስን የረገጠበት ቀን በኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ ኢኒስቲትዩት ዛሬ ተከብሯል።     

በበዓሉ ላይ በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌደሬሽን ኢምባሲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።        

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ሩሲያ በስፔስና ቴክኖለጂ ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት አገር ናት።

አገሪቷ በመስኩ ያካበተችውን ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታካፍል ፍላጎት መኖሩን ጠቅሰው የሁለቱ አገራት የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚቴ በዘርፉ የዕውቀት ሽግግሩ ላይ እየመከረ ነው ብለዋል።     

በተለይም የኒዩክለር ቴክሎጂ በኢትዮጵያ ለኃይል አቅርቦት ግልጋሎት እንዲውል ድጋፍ የሚያመቻች ልዑክ ዛሬ ምሽት ወደሩሲያ እንደሚያቀና አስታውቀዋል።     

በሚኒስትሩ የሚመራው ልዑኩ በሩሲያ ለ4 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከስፔስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የመወያያ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል ነው ያሉት።      

"ሩሲያ በኒዩክለር ቴክኖለጂ፣ በስፔስ አሰሳ እውቀት ያላቸው ሳይንቲስቶች ባለቤት እንደመሆኗ ኢትዮጵያ በጋራ የመስራት ፍላጎት አላት፤ ጠንካራ ግንኙነትም የመፍጠር ቁርጠኝነቱ አለ" ሲሉም ዶክተር ጌታሁን ተደምጠዋል።     

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሩሲያ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በስፔስ ዘርፍ ትብብር እንዳላቸው አመልክተዋል።          

በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጠውን ሥልጠና ሩሲያ የባለሙያ ድጋፍ እያደረገች መሆኗንም አክለዋል።   

"በኢትዮጵያ የማይገኙ ትልልቅ የስፔስ መረጃዎችን ከሩሲያ ጋር ልውውጥ እያደረግን ነው" ያሉት ዶክተር ሰለሞን በአገራቱ መካከል ለስፔስ ምርምር የሚሆን መሳሪያ ድጋፍ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል። 

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1961 አፕሪል 12 ሩሲያዊው ዩሪ ጋጋሪ ለመጀመሪያ ግዜ ስፔስን ረግጧል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅለላ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም ቀኑ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም