የግዢ መመሪያ በመተላለፍ ግዢ የፈፀሙ 59 የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር ዋሉ

101

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2011 የግዢ መመሪያን ተላልፈው ግዢ ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 59 የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የአራት የመንግስት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለሃብቶች ናቸው ተጠርጥረው የተያዙት።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በዋና ዋና ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ እንዳሉት፤ በመንግስት ተቋማት የተፈፀመ ከባድ የሙስና ወንጀል ላይ ላለፉት 3 ወራት ምርመራ ሲደረግ ቆይቷል።

በዚህም በተለይ የመንግስትን መመሪያ ሳይከተሉና ያለአግባብ ግዢ የፈፀሙ አራት የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የመንግስት ግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ ይገኙበታል።

የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚና የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ፣ የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ናቸው።

በተጨማሪም ሌሎች የተቋማቱ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎችን ጨምሮ  በጥቅም የተሳሰሩ ግብረ አበሮችና ባለሃብቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው አቶ ብርሃኑ የተናገሩት።

የመንግስት ግዢ ንብረት አስተዳደርና ማስወገድ ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን የ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በአለም ዓቀፍ ጨረታ በጥቅም በመመሳጠር በመንግስት ኃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ከፍተኛ ኃላፊዎቹ ከ94 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያቀረበ ድርጅት እያለ ያለአግባብ ለሌላ ድርጅት በመስጠታቸው ወደ 19 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያለአግባብ እንዲከፈል አድርገዋል ነው የተባለው።

ይህ በከፍተኛ ዋጋ ስንዴውን ያቀረበው ድርጅት በኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት መጠቀም ሲገባው ባለመጠቀሙ ከመርከብ የሚገኘውን 4 ሚሊዮን ዶላር  ጨምሮ በአጠቃላይ ከ23 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ  ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውም ነው የተብራራው።

ለተለያዩ መስሪያ ቤቶች የኮምፒውተር ግዢ ሲፈፀም የቴክኒክ ግምገማ ያላለፈ የንግድ ድርጅት ህገወጥ በሆነ ትዕዛዝ እንዲያልፍ ተደርጎ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲያደርስና ኮምፒውተሩ በተቋማት ተሰራጭቶ በሚሰራበት ጊዜ ስራው ውጤታማ ሊሆን እንዳልቻለም ተነግሯል።

የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች በመመሳጠር የብረት ክምችትን ታሳቢ ሳያደርጉ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ያለአግባብ የግንባታ ብረት ግዢ እንዲፈፀም ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ለተቋሙ ከፍተኛ ክሊኒክ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችንና መድሃኒቶችን ለመግዛት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም በህዝብና መንግስት ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን አብራርተዋል።

የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲም የግዢ መመሪያን በመተላለፍ ከአንድ አቅራቢ በቀጥታ በድምሩ 79 ሚሊዮን ብር እና 479ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ህገ-ወጥና ከመመሪያ ውጪ የመድሃኒት ግዢ ፈፅሟል ነው የተባለው።

እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ ካቀረበ አቅራቢ ሊገዛ የሚገባውን የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች የእቃ ግዥ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ 92 ሚሊዮን ብር ግዢ እንዲፈፀም በማድረግ መንግስት ላይ ጉዳት መድረሱም ተነግሯል።

ግልፅ ጨረታ በማውጣት ግዢ መፈፀም እያለበት በውስን ጨረታ የ23 ሚሊዮን እንዲሁም ግልፅ ጨረታ መገዛት ሲገባቸው የ24 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የመድሃኒት ግዢ እንዲፈፀም መደረጉም ተብራርቷል።

የመድሃኒት መጋዘን ግንባታ አገልግሎት ተጨማሪ ማስፋፊያ በሚል ከዋናው ጨረታ ከእጥፍ በላይ በመክፈል ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት እንደደረሰም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ተናግረዋል።

በአራቱም ተቋማት በተደራጀ ቡድን በተሰራው ስራ በበቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገው ምርመራ ከገቢ በላይ ኃብት አፍርተው የተገኙ እንዲሁም ቤታቸው ሲበረበር የተለያዩ የቤት ካርታዎችና የባንክ አካውንቶች እንደተገኘና መረጃው እየተጠናቀረ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

አብዛኛው መረጃ የተያዘ በመሆኑ የፍርድ ሂደቱ በፍጥነት እንደሚካሄድም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም