በመጪዎቹ አስር ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ዝናብ ይጠበቃል

47

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 4/2011 በሚቀጥሉት አስር ቀናት በኢትዮጵያ በአብዛኛው ክፍል ከፍተኛ ዝናብ ይጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ገለፀ።

በተለይም የደቡብና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።

በዚህም ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብና የምስራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ ቦረናና ጉጂ ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚያገኙ አካባቢዎች ናቸው።

ከሶማሌ ክልል ሰሜናዊ ክፍል ፋፈን እና ሲቲ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ፣ ጋምቤላ፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዞኖች በመጪዎቹ አስር ቀናት ዝናብ ያገኛሉ።

ከአማራ ክልል የዋግህምራ፣ የደቡብና የሰሜን ወሎ ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የመካከለኛው፣ የምስራቅ፣ የደቡብና የአፋር ዞኖች መደበኛና ከባድ ዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችልም ትንበያው ያሳያል።

በተጨማሪም የምስራቅ ጎጃም፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ጋምቤላ፣ አሶሳና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም የደቡብ ሶማሌ ዞኖች በአብዛኛው መደበኛ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቅ እንደሚሆኑም ይገመታል።

ይህም በተለይ ከእርሻ እንቅስቃሴ አኳያ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በስርጭትና በመጠን ረገድ ጥሩ ዝናብ የሚያገኙበት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።

እንዲሁም የመኸር ወቅት የረዥም ጊዜ ሰብል አብቃዮች የማሳ ዝግጅትና የዘር እርሻ እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ሲሆን የደቡብ ምስራቅ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙበት እንደሆነም እንዲሁ።

የሚጠበቀው ዝናብ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች ጠቀሜታ ሲኖረው ለቋሚ ተክሎችና የውሃ ፍላጎት መሟላት እንዲሁም ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ ለማቆርና ለማጠራቀም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልም ተብሏል።

በመሆኑም በሚቀጥሉት 10 ቀናት አብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ተፋሰሶች ማለትም አባይ፣ ኦሞጊቤ፣ ባሮአኮባ፣ ስምጥሸለቆ፣ በላይኛውና መካከለኛው ተከዜ፣ አፋር ደናክል፣ በላይኛውና በታችኛው አዋሽ፣ በዋቢሸበሌና በገናሌዳዋ የተሻለ እርጥበት ይኖራቸዋል።

በተጨማሪም በጥቂት የታችኛውና የመካከለኛው አባይ እንዲሁም በላይኛው ኢጋዴን አዋሳኝ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ የእርጥበት ኑኔታ እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የተቀሩት ተፋሰሶች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም