የውሃ ሃብታችንን በአግባቡ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ

75

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011 "የውሃ ሃብታችንን በአግባቡ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የተፋሰስ ልማት ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን አሳሳቡ።

ሰብሳቢው ይህን ያሉት የተፋሰስ ልማት ከፍተኛ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።

ጉባኤው በዋናነት የውሃ መጠቀሚያ ታሪፍ የሚወስን ረቂቅ ደንብና በተፋሰስ ልማት ተቋማዊ ማሻሻያ ላይ ተወያይቷል።

የመስኖ ልማት፣ አሳ ማስገር፣ የውሃ ኃይል ማመንጨት፣ ማዘጋጃ ቤታዊ የውሃ አቅርቦትና ከውሃ ሃብት ጋር የተያያዙ መዝናኛዎች  ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ጥቂት ገንዘብ ለተጠቀሙበት ውሃ ታሪፍ እንዲከፍሉ የሚያደርግን ረቂቅ ደንብ  በጉባኤው ይሁንታ አግኝቷል።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በመንግስት የተነደፉ አገርአቀፍ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጦች ካለተፋሰስ ልማት እውን ማድረግ አይቻልም።

በመሆኑን የውሃ ሃብታችንን በተገቢው መልኩ በመንከባከብ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል ነው ያሉት።

በውሃ አጠቃቃም ላይ ታሪፍ መደረጉ ማህበረሰቡ ለውሃ የሚሰጠውን ግምት ከፍ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።

የክፍያ ስርዓቱ ዝቅተኛው ማህበረሰብ ላይ ጫና እንዳያሳድር ደንቡ ገቢራዊ እስኪሆን በጥንቃቄ በየደረጃው መፈተሽ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ታሪፉ ገቢራዊ እስኪሆን ከመስራት ጎን ለጎን ለውሃ ተደራሽነትም ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የተፋሰስ ስራዎችን ወጥነት እንዲኖራቸው ሁሉም የተፋሰስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች በጋራ በአንድ ተቋም እንዲደራጁ ተደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የመረጃ ቅብብሎሽ እንዲኖርም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውሃ አጠቃቀም ላይ የሚደረገው ታሪፍ መንግስት ለዘርፉ ያወጣውን ወጪ ለማካካስ ሳይሆን በዋናነት ውሃን ተንከባክቦ ለማቆየትና ለማህበረሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም