መገናኛ ብዙሃን ከስሜት ኮርኳሪነት ወጥተው ህዝብን የሚጠቅም ሚዛናዊ ዘገባ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

333

አዳማ ሚያዝያ 3/2011 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና   ባለሙያዎች  ከስሜት ኮርኳሪነት ወጥተው  ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ሚዛናዊ ዘገባ እንደሚጠበቅባቸው  የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ገለጹ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር  አዲሱን የግብርና ስትራቴጂና የልማት ፓኬጅ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንዳሉት  መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ከስሜታዊ ዘገባ ይልቅ የሀገሪቱን ልማት ለማፋጠን የሚያግዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አላባቸው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች  የዜጎችን የልማት እይታ ችላ በማለት የህዝቡን ስሜት በሚኮሮክሩ ጉዳዮች ላይ መጠመዳቸውን  ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የተቀዛቀዘውን የልማት ስኬቶችና ማነቆዎች ዘገባ ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ልማቱን የሚያቀጭጩና ህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ እንዳይሳተፍ የሚያደርጉ በፖለቲካ ጉዳዮች ብቻ ያተኮሩ ዘገባዎች የሀገርን ምጣኔ ሀብት በማዳከም ማህበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል አመልክተዋል።

ተቋማቱ ዘገባ ሚዛናዊ በመሆን  በልማት፣በፍትህና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በእኩልነት መዘገብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

“የግብርና ሴክተር ልማትና እድገት ግቡን እንዲመታ የሰው ኃይል የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም መከታተል፣ውጤታማ የመሬት አጠቃቀም እንዲረጋገጥና ምርታማነትን ማሳደግ በሚቻልበት ሂደት ላይ ህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስጨበጥ ዘርፉ ማገዝ ከሚዲያ ባለሙያዎች ይጠበቃል” ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው ባለፉት አስር ዓመታት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን  በማመንጨት በዘርፉ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይም በስንዴ፣ገብስ፣ሽንብራ፣ቦቆሎ፣ማሽላና እንስሳት ሀብት ልማት ዙሪያ በምርምር የሚወጡትን የተሻሻሉ አሰራሮች ለአርሶ አደሩ በማድረስ በኩል የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን አስረድተዋል።

በዚህም የሰብል ምርታማነት በሄክታር በአማካኝ  እስከ 39 ኩንታል መድረሱን ጠቅሰው ይህን  አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘርፉ የመገናኛ ብዙሃን ድጋፍ የታከለበት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ሀገሪቱ በዓመት በአማካይ ከ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለስንዴ ግዥ እንደምታወጣ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ይህን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተሻሻሉ አዳዲስ አሰራሮችን በተገቢው  ለአርሶ አደሩ ማዳረሱ እንዲጠናከር መስራት  እንደሚገባ ጠቁመዋል።