ባለ አራት እግር መኪና - የተማሪው የፈጠራ ውጤት

ጎባ ሚያዝያ 3/2011 በባሌ ዞን ጋሰራ ወረዳ የናቄ ነገዎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በአካባቢው ከሚገኙ የወዳደቁ ዕቃዎች ባለ አራት እግር አነስተኛ መኪና መስራቱ ተጠቆመ፡፡

መኪናዋን የሰራው የናቄ ነገዎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ታዳጊ ወጣት ሳፊ አደም ነው፡፡

እንደ ወጣት ሳፊ ገለጻ መኪናዋን ሊሰራ የቻለው የፈጠራ ስራውን በመጠቀም ከወዳደቁና 60 ሺህ ብር በማይሞላ ወጪ ከአካባቢው ገበያ በቀላሉ ካገኛቸው ዕቃዎች ነው፡፡ 

አምስት ሰው የመጫን አቅም ያላት መኪና በተገጠመላት የሞተር ሳይክል ኢንጂን አማካኝነት በአስፓልትና በጠጠር መንገድ ላይ ስትንቀሳቀስ ታይታለች።

ተማሪው እንዳለው መኪናዋን ሰርቶ ለመጨረስ ስድስት ወራት ጊዜ የፈጀበት ሲሆን በአካባቢው የሚስተዋለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግር የፈጠራ ስራውን በጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል፡፡

ሁሌም ለቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራ እንደሚተጋ የተናገረው ወጣት ሳፊ ከዚህ በፊት በአካባቢው ካገኛቸው ዕቃዎች የገልባጭ መኪና ሞዴል  መስራቱን አስታውሷል፡፡

"ቴክኖሎጂ አፍላቂ ወጣቶቹ ጠንክረው ከሰሩ አገሪቱ ወደፊት ከውጪ ልታስገባ የምትችለውን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መፍጠር ይቻላል" ሲልም ወጣቱ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

ተማሪው እንዳለው ትምህርት ቤቱ ለፈጠራ ስራው በአነስተኛ ወጪ የሚገዙ መሳሪያዎችን እንዲጠቀም ከመፍቀድ ጀምሮ መምህራን በማማከርና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ አድርገውለታል፡፡ 

የናቄ ነገዎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ፈይሳ ከበዳ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚገኘው የቴክኖሎጂ ክበብ አማካይነት የሚሰሩ የፈጠራ ሥራዎች በአይነት፣ በብዛትና ጥራት እያደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በእዚህም የተማሪዎችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክህሎት ለማጎልበት በመምህራኖቻቸው በኩል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

"የተማሪውን የሥራ ውጤት ለማጎልበት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት መብት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል " ብለዋል፡፡

የሕብረተሰቡን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም ለማጎልበት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክበብ መቋቋሙን የገለጹት ደግሞ የባሌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳ ግዛው ናቸው፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በዞኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ወጣቶች በፈጠራ ሥራቸው በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገዙ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ችለዋል፡፡

ተማሪዎቹ በአካባቢያቸው ከወዳደቁ ዕቃዎች ከሰሯቸው የፈጠራ ሥራዎች መካከል የማቀዝቀዥና ማሞቂያ ማሽኖች፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምድጃ፣ የባንክ አሰራርን የሚያቀላጥፍ መሳሪያና ሌሎች ሥራዎች እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም