ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በውጫሌ ወረዳ ለሚገነባው ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

88

ፍቼ ሚያዚያ 3/2011 ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ለሚገነባው ሁለተኛ  ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ፡፡

በወረዳው ቦሶቄ ጃቴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር  ተገኝተው  የመሰረት ድንጋዩን  ያስቀመጡት ቀዳማዊት እመቤቷ  እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ ትውልድን በእውቀት ፣በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት ለማነጽ እንዲያግዝ ይሰራል፡፡

"በተለይ የሰላም መኖር ወጣቶች እንዲማሩ፣ እንዲያድጉና ሀገር እንዲያበለፅጉ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ወገን በአንድነት ለሰላም ሊሰራ ይገባል "ብለዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ግንባታም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ነው የታቀደው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ባይሣ በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ መገንባት መማር እየቻሉ እድል ላጡ ታዳጊ ወጣቶች ሰፊ  እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መንግስት ስም ቀዳማዊት እመቤት ላደረጉት በጎ ስራ አምስግነዋል፡፡

ይህም የአካባቢው  ወጣቶች በመልካም ስነ ምግባር ታንፀው ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት በሰሜን ሸዋ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ካስቀመጡት  በተጨማሪ ቀደም ሲልም በምስራቅና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተመሳሳይ ተግባር እንዲከናወን አግዘዋል፡፡

ግንባታውን የሚያካሂደው የጉዲና ቱምሲና ኘሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ኢዮኤል ዮናስ ትምህርት ቤቱ በሃያ  ሚሊዮን ብር ወጪ  እንደሚገነባና በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ   ዘመናዊ የመማሪያ፣ የቤተ መፃሕፍት፣ የቤተ ሙከራና ሌሎችንም  ክፍሎች በማካተት እስከ 1ሺ500 ተማሪዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጐ የሚገነባ ነው፡፡

ትምህርት ቤቱን ግንባታ ለመጀመው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል ጃቴ በሚል ስያሜ ይታወቅ የነበረው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በአምስት ሄክታር መሬት ላይ  የሚሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ወይዘሮ ማስረሻ  ገብረወልድ ናቸው ፡፡

ለትምህርት ቤቱ የመሰረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ስነሰርዓት ወቅት ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በአካባቢው ሕብረተሰብ የተዘጋጀ የባሕላዊ እቃ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም ቀዳማዊት እመቤት  ለትምህርት ልማት ላበረከቱት በጐ ምግባር አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም