በይርጋ ጨፌ ስቴዲየም የተጠለሉ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋሉ

118

ይርጋ ጨፌ ሚያዚያ 3/2011 ወትሮም ቢሆን ዝናብ እንደማያጣው በሚነገርለት ይርጋ ጨፌ ከማለዳው መከባበድ የጀመረው ሰማይ ረፋድ ላይ ሳይሰስት ያዘለውን ማውረድ ጀምሯል።

በማካፋት የጀመረው ዝናብ በይርጋ ጨፌ ስቴዲየም ለተሰባሰቡት ተፈናቃዮች እንኳን ሳይሳሳ እየበረታ ሄደ።

ከአምስት ቀናት በፊት ነው። በስፍራው የተገኘው የኢዜአ የጋዜጠኞች ቡድን ጀምሮት የነበረውን ቃለ መጠይቅ በዝናቡ ምክንያት ለማቋረጥ ተገደደ።

የኋላ ኋላ የዝናቡን ማቆም ተከትሎ የተቋረጠውን ቀረፃ ለመቀጠል በድጋሚ ወደ ስቴዲየሙ ጎራ ባልን ጊዜም ሜዳው ላይ በርካታ ህፃናትና ሴቶች በእንግድነት የተገኘነውን የቻሉት በእግራቸው ያልቻሉት ደግሞ በአይናቸው ይከተሉን ጀመር።

በሁሉም ዘንድ የተለያየ ስሜት ይነበባል፤ ለቅሶ የሚቀድማቸው ህፃናትም የበዙ መሆናቸውን ከጆሯችን በላይ ነጋሪ አላሻንም።

በመቀጠልም ፈንጠር ብላ ተቀምጣ በትካዜና ጭንቀት ውስጥ እንዳለች ወደ ገመትናት ወይዘሮ ማይካችንን አስጠጋን፤ የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር በመሆኗ የምጥ ስሜት እንደጀመራት ነገረችን።

ለመውለድ ሰዓታትን እየቆጠረች የምትገኘው ወይዘሮ ታመነች አስራት የተፈናቀለችው ከምእራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ሶኬ ቀበሌ ሲሆን በስቴዲየም ቆይታዋ የሚቀመስ ለማግኘት እንደከበዳት ነገረችን።

ከቀርጫ ወረዳ ጋሌሳ ዱቢሳ ቀበሌ መፈናቀላቸውን የገለጹልን አቶ ግርማ ጎዳናም በተመሳሳይ በይርጋ ጨፌ ስታዲየም የተሰበሰበው ህዝብ መቸገሩን ይገልጻሉ፤ በመሆኑም መንግስት አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በስፍራው የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ያገኘነው የጤና ባለሙያ ትእግስቱ መንገሻ በህፃናትም ይሁን በአዋቂዎች ዘንድ የተቅማጥና ትውከት ታማሚዎች መበራከታቸውን ይናገራል።

ዝናቡ እየጠነከረ ከሄደም በሽታው እንደይባባስ ተፈናቃዮቹ ከወዲሁ እልባት የሚያገኙበትን አማራጭ መፈለግ እንደሚገባ አሳስቧል።

የይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብራሃም ሆርዶፋ በበኩላቸው ተፈናቃዮቹ እስካሁን ተገቢ ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገልጸውልናል።

እንደ አቶ አብራሃም ገለፃ ተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ እገዛ እያገኙ ያሉት የይርጋ ጨፌ ከተማና የወረዳውን ህዝብ በሚያደርገው ልገሳ ነው።

ይህ ደግሞ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ነግረውናል።

የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋም በይርጋ ጨፌ ስቴዲየም ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ድጋፉ መዘግየቱን አምነዋል።

ሆኖም አሁን ከመንግስት የተጠየቀው እርዳታ ወደ ስፍራው በመድረስ ላይ መሆኑን ነግረውናል።

እንደ አቶ ገዙ ገለፃ ይህንን ዜና እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ በዞኑ አጠቃላይ ከ450 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች አሉ።

ከይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም ላለፉት 15 ቀናት በይርጋ ጨፌ ስታድየም ከ14 ሺህ 400 በላይ ዜጎች ተጠልለው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም