ከአማራ ክልል የግብርና ባለሃብቶች በውላቸው መሰረት እያለሙ ያሉት ከ25 በመቶ እንደማይበልጡ ተገለጸ

58

ባህርዳር  ሚያዝያ 3/2011 በአማራ ክልል በግብርና ኢንቨትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች በውላቸው መሰረት እያለሙ ያሉት ከ25 በመቶ እንደማይበልጡ የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ገለጸ።

ባለሃብቶቹ በበኩላቸው በአካባቢው እየተፈጠረ ያለው የፀጥታ ስጋት፣ የመሰረተ ልማት እጦትና የቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረት ፈተና ሆኖብናል ብለዋል።

በቢሮው ባዘጋጀውና በባህርዳር ከተማ ከባለሃብቶቹ ጋር በተካሔደው የምክክር መድረክ ላይ በቢሮው የኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ እንደገለፁት በክልሉ አንድ ሺህ 495 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተዋል።

ባለሃብቶቹም በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በደን ልማት፣ በቅመማቅመም፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በአበባ ልማት፣ በንብ ማነብና ሌሎች የልማት ዘርፎች ለመሰማራት ከ233 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

“ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ባለሃብቶች የተሰጣቸውን መሬት ጦም በማሳደር፣ ለሌላ በማከራየት፣ ከአካባቢው አርሶ አደር በታች የሚያለሙ ናቸው”ብለዋል፡፡

“ተደጋጋሚ ድጋፍ ተደርጎላቸው መስተካከል ያልቻሉና ፈቃዳቸውን ያላሳደሱ 134 ባለሃብቶችን በመለየትም የተረከቡትን 14 ሺህ ሄክታር መሬት በመንጠቅ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል”ብለዋል።

አሁንም በአግባቡ እያለሙ ያልሆኑ ሌሎች 357 ባለሃብቶችም በውላቸው መሰረት ወደ ልማት  እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከባለሃብቶች መካከልም 25 በመቶ የሚሆኑት የተሰጣቸውን መሬት ለአካባቢው አርሶ አደር ምሳሌ ሊሆንና የዕውቀት ሽግግር ሊያመጣ በሚችል መልኩ ተንከባክበው እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“በክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንቱ በሚጠበቀው ልክ እያደገ አይደለም” ያሉት ዳይሬክተሩ “በቀጣይ ችግሮችን በመለየት ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል”ብለዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ 100 ሄክታር መሬት ወስደው በሰብል ልማት እንደተሰማሩ የተናገሩት አቶ አንጋው ሙላት በበኩላቸው በተረከቡት መሬት ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ጥጥና ሌሎች ሰብሎች እያለሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በተከሰተው የፀጥታ ችግር የእርሻ እንቨስትመንቱን በአግባቡ ለመከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የሰራተኛ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት ችግር፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የባለሙያ የድጋፍና ክትትል ዕጥረትም ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በአካባቢው የሚገኝ አብዛኛው ባለሃብት ለኪሳራ መዳረጉን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ማስተዋል ማዘንጊያ ናቸው።

የፀጥታው ችግር ባይወገድም ችግሩን ተቋቁመው ላመረቱት ምርት የክልሉ መንግስት የገበያ ትስስር በመፍጠር እየደገፋቸው ባለመሆኑ ውጤታማ ሊሆኑ እንዳልቻሉም አስረድተዋል።

በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መስፍን ክፍሉ በበኩላቸው በሰላሙ መደፍረስ ምክንያት ንብረታቸው መውደሙን ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው እንደገለጹት የተፈጠረው አለመረጋጋት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እተየሰራ ነው።

“የፀጥታ ችግሩ በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽህኖ ከባድ ነው” ያሉት ኃላፊው “ምቹ ሁኔታም እያለ የተረከቡትን ቦታ በአግባቡ የማያላሙ ባለሃብቶች አሉ” ብለዋል፡፡

“ለባለሃብቱ ዋነኛ ማነቆ የሆኑ የሰላም፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የብድርና የግብአት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር፣ የድጋፍና ክትትል ችግሮች እንዲቃለሉ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል”ብለዋል።

ባለሃብቱ በተለይ ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ በማሸጋገር፣ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ጥራት ያለው ምርት ማምረት ብቻ ሳይሆን በልማቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡

በቀጣዩ የምርት ዘመን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የነበረባቸውን ችግር በማቃለል የወሰዱትን መሬት ለማልማት ከወዲሁ ዝግጅት አድርገው ወደ ልማቱ እንዲገቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም