የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ በቁጥጥር ሥር ዋለ

104

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 3/2011 የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ በእንግሊዝ ርዕሰ ከተማ ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ጁሊያን አሳንጅ በስዊድን መንግሥት የወጣበትን የጾታ ጥቃት ክስ ለመሸሽ በኢኳዶር ኤምባሲ ለሰባት ዓመታት ያህል ተደብቆ ቆይቷል።

አሳንጄ በቁጥጥር ሥር የዋለው ኤምባሲው ተጠርጣሪውን ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ባለመሞከሩ ነው ተብሏል።

ይህም የዌስት ሚኒስቴር ማጀስትሬት ፍርድ ቤት እአአ በ2012 ባወጣበት የእስር ማዘዣ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢኳዶር ፕሬዚዳንት ሌኒን ሞሬኖ ተጠርጣሪው ዓለም አቀፍ ሥምምነትን በተደጋጋሚ በመተላለፉ ያቀረበውን ጥገኝነት ማቋረጡም ለመታሰሩ ምክንያት ነው ተብሏል።

በአንጻሩ ዊክሊክስ የኢኳዶር መንግሥት ለአሳንጅ ያቀረበውን ጥገኝነት ማቋረጡን ዓለም አቀፍ ሕግን መተላለፍ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ዛሬ የአሳንጄ መታሰር ዊክሊክስ ከቀናት በፊት በአሳንጄ ላይ ድብቅ ስለላ መካሄዱን ማውጣቱን ተከትሎ መሆኑን ተዘግቧል።

አሳንጄና የኢኳዶር ባለሥልጣናት አሳንጄ ምን እንደተፈቀደለትና ምን እንዳልተፈቀደለት በተመለከተ እሰጣ ገባ ውስጥም እንደነበረ ገልጿል።

በመጨረሻም አሳንጄ በቁጥጥር ሥር ውሏል፤ እሱም "ኤምባሲውን ጥዬ ለመሄድ አልፈልግም፤ ምክንያቱም ወደ አሜሪካ ልከው በዊክሊክስ ዙሪያ ጥያቄ ያስነሳብኛል" ብሏል።

አሳንጄ ከዚህ በኋላ በማዕከላዊ ለንደን ፖሊስ ጣቢያ እንደሚቆይና ከሰዓታት በኋላም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመራ መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም