በመጋቢት ወር የአኩሪ አተር ግብይት በመጠን 46 በመቶ በዋጋ 47 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ

180

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2011 ባሳለፍነው የመጋቢት ወር የአኩሪ አተር ግብይት በመጠን 46 በመቶ በዋጋ 47 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በቅርቡ ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርዓት የገባው አኩሪ አተር በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም የተካሄደው ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

በዚህም 21 ሺህ ቶን አኩሪ አተር በ282 ሚሊዮን ብር ግብይት የተፈጸመ ሲሆን አማካይ የግብይት ዋጋውም ከየካቲት ወር ጋር ሲነጻጸር በ0ነጥብ23 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

በአጠቃላይ ግብይቱም በመጠን 25 በመቶ ድርሻ ይዟል ነው የተባለው።

ምርት ገበያው በመጋቢት ወር በነበሩት 21 የግብይት ቀናት 30 ሺህ 216 ቶን ቡና፣ 26 ሺህ 390 ቶን ሰሊጥ፣ 21 ሺህ 395 ቶን አኩሪ አተር፣ 6 ሺህ 245 ቶን ነጭ ቦለቄና 25 ቶን አረንጓዴ ማሾ በጠቅላላው በ3ነጥብ6 ቢሊዮን ብር መገበያየቱን አስታውቋል።