በወላይታ ዞን ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ችግር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ

218

ሶዶ ሚያዝያ 3 / 2011 በወላይታ ዞን  እየጨመረ  ለመጣው የተማሪዎች ውጤት መቀነስ  ችግር መፍትሄ እንደሚሻ ተጠቆመ፡፡

የዞኑ የትምህርት አስተዳደር 16ኛ መደበኛ ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዚህ ወቅት የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ እንደገለጹት የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት  ምሳሌ የነበረው የወላይታ ዞን የተማሪዎች ውጤት እየቀነሰ መጥቷል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት የታየው  ዝቅተኛ የአፈጻጸም ውጤት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ የውጤት ማሽቆልቆል የገጠማቸውን ወረዳዎች በመለየት የማስተባበር፣ መምህራንን በማነሳሳት፣ ድጋፍ  እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር የትምህርት ባለሙያዎችን፣መምህራንን፣ወላጆችንና ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት ለመፍትሄው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በዞኑ ኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የትምህርት ሱፐርቪዥን ባለሙያ አቶ ጳዉሎስ ነጋ በበኩላቸው ባልተለመደ መልኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተማሪዎች ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ትኩረት ማነስ፣የጸጥታ ችግሮች፣ በዓላትን ምክንያት በማድረግ  ከትምህርት ገበታ መቅረት ለውጤታቸው  መቀነስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የዘርፉ ባለሙያዎችና መምህራን በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ፈጥነው ወደስራ አለመግባት፣የወላጆች ተሳትፎ ማነስ፣ ኩረጃና  መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሄደው ርቀት አነስተኛ መሆኑ ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ምክንያቶች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በጉኑኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት አለምሐይ ዳሪሎ ናቸው፡፡

በውጤት ማሽቆልቆሉ ምክንያት ከተወቃሽነትና ተጠያቂነት ለመዳን መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እየሰሩ መሆናቸው ጠቁመዋል።

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ላብሶ ባለፈው ዓመት የመሰናዶ ፈተና ከወሰዱ 16ሺህ 964 ተማሪዎች ውስጥ 975ቱ ብቻ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት  ለመምህራን የስራ ላይ ስልጠናዎች መስጠት፣የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት፣ የተማሪዎችን ማቋረጥና ብክነትን ለማስወገድ የወላጆችን ተሳትፎ የማሳደግና የትምህርት አመራር ብቃትን ማሻሻል  ላይ በማተኮር እየሰሩ መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡

ከ1 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የማጣቀሻ መጽሐፍትና ሌሎች ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር መከናወኑን ጠቁመዋል።

ከ500 በላይ የመምህራን ቅጥር መፈጸሙን ያመለከቱተ  ኃላፊው “ከ3 ሺ በላይ ለሆኑ መምህራን የስራ ላይ ስልጠና ተሰጥቷል” ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤው  የተሻለ እንቅስቃሴ ላሳዩ መምህራን፣ ባለሙያዎችና ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡