ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወለጋ ስታዲየምን መረቁ

59

አዲስ አበባ ሚያዚያ 3/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የወለጋ ስታዲየምን መርቀው ከፈቱ።

ስታዲየሙ በግንባታዉ አይነቱ ልዩና የገዳ ስርአትን 8 ዙር ቅርፅ ይዞ የተገነባ መሆኑ ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ስታዲየሙ በምእራብ የኢትዮጵያ ክፍል ስፖርት መነቃቃት ጉልህ  አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

''ወለጋ አገሪቱ በድርቅ በተጠቃችበት ጊዜ ሌላውን ማህበረሰብ ያስጠለለ አካባቢ ነው'' ያሉት ዶክተር አብይ፤ ''ምስራቅ ወለጋን ማልማት ምዕራቡን የአገሪቱ ክፍል በልማትና በንግድ ማስተሳሰር ነው'' ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ በበኩላቸው አንድነትና ህዝባዊ ትብብር ካለ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል የወለጋ ስታዲየም ማሳያ ነው ብለዋል።

ከእኛ አልፎ ለሌላው የምትተርፍ ኦሮሚያን ለመፍጠር ከአካባቢው ልማት መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የስታዲየሙ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ገመዳ በ1999 ዓ.ም የተጀመረው የወለጋ ስታዲየም የመንግስትን እጅ ሳይጠብቁ ህዝብ በራሱ ተሳትፎ ፕሮጀክት ቀርፆ ሰርቶ ማስመረቅ እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። 

የወለጋ ስታዲየም በዝቅተኛ ዋጋ በስርአት በመገንባቱ ልዩ የሚያደርገዉ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል። 

ለስታዲየሙ ግንባታ እስካሁን 196 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በቀጣይ የወንበርና ሌሎች የማጠናቀቂያ ወጪዎችን ሲጨምር 226 ሚሊዮን ብር ወጪ ይሆንበታል ተብሎ ይገመታል።

እስካሁን የህብረተሰቡ ተሳትፎ 48 ሚሊዮን ብር ለስታዲየሙ ግንባታ ውሏል።

ስታዲየሙ 30 ሺህ የተመልካች ወንበሮች ያሉት ስቴድየሙ 17  የስፖርት አይነቶችን ያስተናግዳል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም