በምስራቅ ወለጋ ዞን የኮምቶ ጥብቅ የመንግስት ደንን ከጥፋት ለመታደግ ለሕብረተሰቡ ጥሪ ቀረበ

120
ነቀምቴ ግንቦት 26/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋዩ ቱቃ ወረዳ የሚገኘውን ኮምቶ ጥብቅ የመንግስት ደን ከጥፋት ለመታደግ የአካባቢው ሕብረተሰብ የድርሻውን እንዲወጣ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አቀረበ። ዩኒቨርሲቲው የደን ሀብቱን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በነቀምቴ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በመድረኩ ላይ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴከኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሂርጳ ለገሰ እንዳስታወቁት በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኘው የኮምቶ ደን ላለፉት 24 ዓመታት በሕብረተሰቡ ጉዳት ደርሶበታል። በደረሰበት ከፍተኛ ጭፍጨፋና ምንጣሮ ምክንያት 9 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ከነበረው ደን ውስጥ በአሁኑ ወቅት 68 በመቶው መራቆቱን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ሂርጳ ገለጻ የኮምቶ ደን ያለበት ደረጃ፣ እያጋጠመው ያለው ችግርና በወደፊት እጣ ፋንታውና መፍትሄው ላይ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተካሂዷል። በተለይ የደኑ ሀብት ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ  የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የአካባቢው ሕብረተሰብ የደኑን ሀብት በአግባቡ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። የጉቶ ጊዳ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ጫሊ በሰጡት አስተያየት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት የደን ሀብቱን ለመታደግ ወሳኝ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ቢሮው ጥረት ያደርጋል። ከውይይት መድረኩም የአካባቢውን ደንና መሬት ባለመንከባከብ እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ለመከላከል ጠቃሚ ግብዓት መገኘቱንም ተናግረዋል። የዋዩ ቱቃ ወረዳ የዳሎ ኮምቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍቅሩ ያደታ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የደን ሀብት ሳይመናመን በፊት በአካባቢያቸው ዝናብ በወቅቱ እንደሚያገኙና ንብ በማነብ ሥራ ተሰማርተው ጥሩ ምርት ያገኙ አንደነበር አስታውሰዋል። ከጊዜ ወደጊዜ የደኑ ሀብት እየተመናመነ ሲመጣ ከብቶቻቸው በበጋ ወቅት ለፀሐይ ከመዳረጋቸው ባለፈ በቂ የሣር ግጦሽ በማጣት እየተቸገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አዕዋፍና የዱር እንስሳት በአሁኑ ወቅት ደኑን ለቀው መጥፋታቸውን የሚናገሩት አቶ ፍቅሬ፣ የደኑን ሀብት መልሶ ለማልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ደኑን መልሶ ለማልማት ያደረገውን ጥናት ወደ ተግባር እንዲቀየር ከራሳቸው ባለፈ የአካባቢውን ሕብረተሰብ አሳምነው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ትናንት በተካሄደ የውይይት መድርኩ ላይ የኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት ኢንትርፕራይዝ፣ የአካባቢ ጥበቃና የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣንን ጨምሮ ከ100 በላይ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። በቀጣይ በባለድርሻ አካላት የሚከናወኑ ሥራዎችን የሚከታተሉና የሚገመግሙ ኮሚቴዎች በመድረኩ መቋቋማቸው ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም