በዞኑ ሀሰተኛ የትምህርትና የስራ ልምድ ማስረጃዎች ሲጠቀሙ የተገኙ ሰራተኞች ለህግ ሊቀርቡ ነው

256

አምቦ ሚያዝያ 2/2011 ሃሰተኛ የትምህርትና የስራ ልምድ ማስረጃዎችን በመጠቀም ተቀጥረው የተገኙ 152 የመንግስት ሰራተኞች ለህግ ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆናቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና  የሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

እነዚህ ሰራተኞች ተቀጥረው የተገኙት በተለያዩ የመንግስት የስራ መደቦች ላይ ነው፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ አገኘሁ አጀማ እንደገለጹት የመንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ለማጣራት በተደረገው እንቅስቃሴ 1ሺህ 941 ሰራተኞች ላይ ጥቆማ ደርሷቸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል 152 ሰራተኞች ከተለያዩ ኮሌጆች የተመረቁ በማስመሰልና ባልሰሩበት መስሪያ ቤት የስራ ልምድ በማስያዝ  ተቀጥረው ተገኝተዋል፡፡

ማስረጃቸው ሀሰተኛ መሆናቸው የታወቀውም  ተምረው ተመርቀዋል ከተባሉት ኮሌጆችና ከሚሰሩበት ድርጅቶች ጋር በመሆን በማጣራቱ እንደሆነ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡

ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል 95 ሰራተኞች ያልተመረቁበትን ማስረጃ ያቀረቡ ሲሆን 57 ደግሞ የውሽት የስራ ልምድ አቅርበው እየሰሩ የተገኙ ናቸው፡፡

የ14 ድርጅቶችና ኮሌጆች አድራሻ ማግኘት ባለመቻሉ በክልሉ ዋናው መስሪያ ቤት  በኩል እንዲጠራ ማስተላለፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

” ተጠርጣሪ  ሰራተኞች ለህግ ለማቅረብ ማስረጃ በመገኘቱ ክስ ለመመስርት በሂደት ላይ ነን” ብለዋል፡፡

የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሰራተኛ  ወይዘሮ ሻሜ  በቀለ በሰጡት አስተያየት የሀሰት የትምህርት ማስረጃን በመጠቀም መስራት  የመንግስትን ስራ በማበላሸት በህብረተሰቡ  ቅሬታ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

” በሀሰተኛ ማስረጃ የሚሰሩ ሰራተኞች በራስ የመተማመን ብቃት ሰለሌላቸው ሌሎች ሰራተኞችን ስለሚጎዱ ሁሉም ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን መሆን አለበት “ያሉት ደግሞ የዞኑ ን ግብርና ጽህፈት ቤት ሰራተኛ ወይዘሮ ሶሬቲ ቤለማ  ናቸው።

በሀሰተኛ  ማስረጃዎች ያለብቃት የሚጠቀሙ ሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ  ስለሚያደርጉ  ጥቆማ በመስጠት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።