ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ላይ አሻሽሎ ባቀረበው ክስ ላይ መቃወሚያ ለመስማት ቀጠሮ ሰጠ

105

አዲስ አበባ ሚያዝ 2/2011 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ላይ አሻሽሎ ባቀረበው ክስ ላይ መቃወሚያ ለመስማት ለሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጥሮ ሰጠ።

በእነ ቴዎድሮስ አዲሱ የክስ መዝገብ አንደኛ አቶ አብዲ ዩሱፍ መሐመዶ (ያልተያዙ)፣ ሁለተኛ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ፣ ሦስተኛ አቶ መሐመድ አህመድ (ያልተያዙ) እና አራተኛ አቶ አብዱላሂ ሁሴን (ያልተያዙ) ይገኙበታል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው የሱማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሱማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤት ከሆኑት ከአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ጋር በገባው ውል መሰረት ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 578 ሺህ 274 የመማሪያ መጻህፍትን በ18 ሚሊዮን 990 ሺህ ብር አሳትሞ ለማቅረብ የግዥ ውል ገብቷል።

ሁለተኛ ተከሳሽ የግዢ ውል የገባ ቢሆንም ስራው ሳይሰራ ከቀድሞው ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እና ከቀድሞው ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የፋይናንስና ሎጅስቲክስ የሥራ ሂደት ኃላፊ ጋር በመመሳጠር የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና አላግባብ ተከፍሎታል።

በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ በፌዴራል መንግስት በተመዘገበ ህዝባዊ ድርጅት (ኒያላ ኢንሹራንስ) አሰራርና መመሪያ ውጭ አላግባብ ዋስትና በመስጠት፤ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ ለ2ኛ ተከሳሽ አላግባብ 15 ሚሊዮን 306 ሺህ 803 ብር ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የክሱ ዝርዝር ያስረዳል።

አለአግባብ የተከፈለው ገንዘብ እንዲመለስ፣ መጽሕፍቱም ታትመው እንዲገቡ ባለማድረግ 2ኛ ተከሳሽም ከመንግስትና ህዝባዊ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥሮ አለአግባብ ዋስትና እንዲሰጠው በማድረግ ክፍያ በመውሰድ መጽሕፍቱም ባለመቅረባቸው በህዝብና መንግስት ገንዘብ እንዲሁም በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ዐቃቤ ህግ በክሱ ገልጿል።

ተከሳሽ አለአግባብ በተከፈለው ገንዘብ በተከፈተ የባንክ ሂሳብ በቂ ገንዘብ የሌለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቼክ አስቀድሞ ለቅድሚያ ክፍያ ዋስትና የተያዘ በማስመሰል ለኢንሹራንሱ በዋስትና እንዲያዝ መደረጉንም ጠቁሟል።

በመሆኑ 1ኛ፣ 3ኛና 4ኛ ተከሳሾች የመንግስትንና ህዝባዊ ድርጅትን ሥራ በማያመች ሁኔታ በመምራት፣ 2ኛ ተከሳሽም በመንግስትና በህዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች እና ኃላፊዎች በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ልዩ ተካፋይ በመሆን በመንግስትና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ ሁሉም ተከሳሾች አባሪ ተባባሪ በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከኒያላ ኢንሹራንስ ጋር በተያየዘ ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ ተላልፏል ያለውን የግዢ እና የኢንሹራንስ መመሪያ ክስን በግልጽ በማሳየት አሻሽሎ ለዛሬ ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ዐቃቤ ህግ ዛሬ ተከሳሽ ከግዢ እና ከኢንሹራንስ መመሪያ ጋር በተያያዘ ያለውን ክስ አሻሽሎ አቅርቧል።

ተከሳሽ ቴዎድሮስ አዲሱ በተሻሻለው ክስ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመስማት ለሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጥሮ ሰጥቷል።

መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በነበረው ችሎት ተካሳሽ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ''የተከሰስኩት በሶማሌ ክልል የትምህርት ቢሮ የመጽሐፍት ህትመትን በተመለከተ በመሆኑ ክሱ በክልሉ እንዲታይልኝ'' ሲሉ ጠይቀው ነበር።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ አቃቤ ሕግ ካቀረበው ማስረጃ ውስጥ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ መጽሐፉ የሚታተመው በክልሉ በጀትና በፌዴራል መንግስት ድጎማ በመሆኑ ጉዳዩ የፌዴራል መንግስት መሆኑን ያሳያል በማለት መቃወሚያውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለጊዜው ስልጣኑ በመነሳቱም የአቶ ቴዎድሮስ ጉዳይ መታየት ያለበት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆን እንዳለበት መወሰኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም