ኔዘርላንድስ ለህፃናት ሆስፒታል ግንባታና የግብአት አቅርቦት የሚውል የ27 ነጥብ 44 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገች

142

አዲስአበባ ሚያዝያ 2/2011 የኔዘርላንድስ መንግስት በአለርት ማዕከል ለሚገነባው ዘመናዊ የህጻናት ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታና ለግብአት አቅርቦት የሚውል የ27 ነጥብ 44 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ድጋፍ አደረገ።

የእርዳታ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበና በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ቫን ሎስድሬክት መካከል ዛሬ ተፈርሟል።

በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው የሚጀመረውና  55 ሚሊዬን ዩሮ የሚጠይቀው 'አዲስ የህፃናት ሪፈራል ሆስፒታል' ከ300 በላይ ልዩ የህፃናት መኝታ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል።

ሁለት ዓመታት በሚወስደው የሆስፒታሉ ግንባታ ከመንግስት በተጨማሪ የግል ኩባንያዎች በገንዘብና በቴክኒክ ድጋፍ አንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንዳሉት፤ ኔዘርላንድስ ለግንባታው ያደረገችው የ27 ነጥብ 44 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል።

በኢትዮጵያ ከ130 በላይ አነስተኛና መካከለኛ የሆኑ የኔዘርላንስ ካምፓኒዎች በተለያዩ የኢኮኖሚ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአለርት የሚገነባው አዲስ የህፃናት ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቆ ስራ ሲጀምር በኢትዮጵያ የሚሰጠውን የህክምና ጥራትና ቀልጣፋ አገልግሎት  ችግር እንደሚያሻሽል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ለሆስፒታሉ ንግባታ የኢትዮጵያ መንግስት 20 ሚሊዮን ዩሮ እንደተመደበ የገለጹት አቶ አድማሱ፤ ''የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት ግንባታ መሆኑ በቀጣይ የግሉን ዘርፍ ለመሳብ ያግዛል'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ቫን ሎስድሬክት በበኩላቸው እርዳታው አገራቸው በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የምታከናውናቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውን የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማጎልበት ኔዘርላንድስ ሁሌም ድጋፍ እንደምታደርግ የገለጹት አምባሳደሩ፤ የህፃናት ሆስፒታሉ ስራ በተሻለ ጥራት እንዲጠናቀቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

''የገንዘብ እርዳታው ከግንባታ በተጨማሪ ለየተለያዩ የሆስፒታሉ ግብዓቶች የሚውል ጭምር በመሆኑ ስልጠናና የጥገና አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ እናደርጋለን'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም